ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የጥቅማችን፣ የክብራችን የነጻነታችን ዋስትና የሆነች አገር ለመገንባት የምናደርገውን ርብርብ ማጠናከር አለብን- አቶ ታዬ ደንደአ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የጥቅማችን፣ የክብራችን የነጻነታችን ዋስትና የሆነች አገር ለመገንባት የምናደርገውን ርብርብ ማጠናከር አለብን- አቶ ታዬ ደንደአ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2015(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የጥቅማችን፣ የክብራችንና የነጻነታችን ዋስትና የሆነች አገር ለመገንባት የምናደርገውን ርብርብ ማጠናከር አለብን ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ገለጹ።
በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን መፍጠር አላማ ያደረገ የፓናል ውይይት ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።
“አገራዊ ማንነት ለጠንካራ አገር ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ የተከናወነው ውይይት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የሰላም ሚኒስቴር ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ አገር የዜጎች ነጻነት፣ ሰላም፣ ክብርና ጥቅም ሁሉ መሰረት መሆኗን ጠቅሰው አገር የሌለው ሰው ምንም ያህል ሀብት ቢኖረው ክብርና ነጻነት ሊኖረው አይችልም ብለዋል።
በትላልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በዜጎች እንዲሁም በልሂቃን መካከል ጠንካራ መግባባትን መፍጠር ለአገራዊ ማንነት ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የጋራ ማንነቱን ጠንቅቆ ያልተረዳ ሕዝብ ስለ ትናንት ታሪኮቹ፣ ስለ ጋራ ጥቅሞቹ፣ ስለ መልካም እሴቶቹና ስለ ነገ ዓላማዎቹ በትክክል ሊያውቅ እንደማይችልም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ከዚህም አኳያ ዜጎች አንድነታቸውን በማጎልበት የጥቅማቸው፣ የክብራቸውና የነጻነታቸው ዋስትና የሆነች ጠንካራ አገር መገንባት የሚችሉት የጋራ ማንነታቸውን በትክክል ለይተው ሲያውቁ ነው ብለዋል።
ጠንካራ የአገር ግንባታ የሕዝቡን ጠንካራ አንድነት ይጠይቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የሕዝብ አንድነት ደግሞ ከምንም በላይ የዜጎች የጋራ ማንነት ላይ ይመሰረታል ሲሉም አስረድተዋል።
በአንድ አገር ዜጎች መካከል የጋራ መግባባት መኖር አለመኖር ብዙ ነገሮችን ይወስናል ሲሉም ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።