የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የትብብር ስምምነቶች የአገራቱ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት እያደገ መምጣቱን ማሳያ ነው- አንጋፋ ዲፕሎማቶች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የትብብር ስምምነቶች የአገራቱ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት እያደገ መምጣቱን ማሳያ ነው- አንጋፋ ዲፕሎማቶች
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 24/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የትብብር ስምምነቶች የአገራቱ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት እያደገ መምጣቱን እንደሚያሳይ ዲፕሎማቶች ገለጹ፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼኽ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በኢትዮጵያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያሳድጉ 17 ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ከፍተኛ አማካሪ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በቀይ ባህር እንዲሁም በፐርሽያን ባህረ ሰላጤ በኩል ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ካላቸው ሀገሮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች የምትገኝ እና በአፍሪካ የጂኦ-ፖለቲካ ተጽዕኖ ያላት ስትሆን፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደግሞ በ40 ዓመት ውስጥ በአሸዋ የተሞላውን በረሀማ መሬት ወደ ልማት በመቀየር የዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር መሆን ችላለች ብለዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነት የሀገራቱን የቆየ ወንድማማችነትና የትብብር ታሪክ መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ፕሬዝዳንት ሼኽ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የተፈረሙ የትብብር ስምምነቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂያዊ ትብብር እያደገ ስለመምጣቱ ማሳያ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በበኩላቸው፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢትዮጵያ ችግር ላይ በነበረችበት ወቅት ከጎኗ የተገኘች የቁርጥ ቀን ወዳጅ መሆኗን ገልፀዋል፡፡
"በአሁኑ ወቅት በአንድ ወይም በሁለት ኃያላን ሀገራት የበላይነት የሚመራ ዓለም የለም" ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ከዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ አገራት ጎራ መቀላቀሏን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ጠንካራ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አለባት ብለዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር መጠናከር፤ ንግድና ኢንቨስትመንትን ከማሳለጥ ባለፈ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ያደርጋል ነው ያሉት፡፡