ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ የፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል 


አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 24/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ከታንዛንያው ጄኪቴ ኩዊንስ ጋር ያደርጋል።

የሁለቱ ክለቦች ፍጻሜ ጨዋታ በዩጋንዳ ንጄሩ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ንግድ ባንክ በግማሽ ፍጻሜው የኬንያውን ቪሂጋ ኩዊንስ 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜው ቀርቧል።

ተጋጣሚው ጄኪቴ ኩዊንስ በግማሽ ፍጻሜው የብሩንዲውን ቡጃ ኩዊንስን 3 ለ 1 ማሸነፉ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድሩ አሸናፊ ከሆነ የሴካፋ ዞንን ወክሎ በኮትዲቭዋር አቢጃን በሕዳር ወር 2016 በሚካሄደው ሶስተኛው የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል።

ከፍጻሜው ጨዋታ ቀደም ብሎ ከቀኑ ስድስት ሰዓት የኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስና የብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ  የደረጃ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም