ቀጥታ፡

በተያዘው ክረምት ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ተደርጓል - የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 24/2015 (ኢዜአ) ፦በተያዘው ክረምት እስካሁን ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ መደረጉን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም ገለጹ፡፡ 

በቀጣዮቹ ሶስት ሳምንታትም ተጨማሪ የሰብአዊ ድጋፎችን ወደ ክልሎች ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።  

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተለያዩ አካባቢዎች ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በክልሎች ለተፈናቃዮች ተደራሽ ለማድረግ በባለፈው ወር ከመንግስት መጠባበቂያ ሃብት ለ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የሚሆን የሰብዓዊ ድጋፍ መላኩን ተናግረዋል። 

የሰብዓዊ ድጋፉ ከዚህ በፊት በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት የፋይናንስ ድጋፍ የሰብዓዊ ድጋፍ በሚሰጡ አጋሮች ጭምር በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች በመድረስ መሰራጨቱን ገልጸዋል።

የሰብዓዊ ድጋፉም የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተዳራሽ ይሆናል ነው ያሉት።፡

በፌደራል መንግስት፣ በክልሎችና በማህበረሰቡ አቅም በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ሆኖም ዜጎች በአካባቢዎቻቸው የሚገኙ ጸጋዎችን በመጠቀም ከተረጂነት ለመላቀቅና ራሳቸውን ለመቻል ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።

በየአካባቢው የሚገኙ አመራሮችም ዜጎች በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በመለየት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምዝገባ ለማድረግ በመንግስት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም