የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በሁሉም መስክ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል- አምባሳደር ጀማል በከር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በሁሉም መስክ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል- አምባሳደር ጀማል በከር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 24/2015 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ እና የፓኪስታን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በሁሉም መስክ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ገለጹ።
በፓኪስታን ኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ስራ የጀመረበትን አንደኛ አመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብሯል።
የሁለቱን አገሮች የዲፕሎማሲ ግንኙነትና በትብብር እያደረጓቸው ያሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ኢዜአ በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከርን አነጋግሯል።
አምባሳደሩ በማብራሪያቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተለይም ከለውጡ ወዲህ በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበለጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ የትብብር ማዕቀፎች በመተግበር ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ላይ ይደረጉ የነበሩ ያልተገቡ የውጭ ጫናዎችን በመቃወም ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጎን መሆኗን በተግባር ማሳየቷንም አምባሳደሩ አስታውሰዋል።
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና ሌሎችም ዘርፎች ትብብራቸው እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን ካራቺ በራራ መጀመሩም ለሁለቱ አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከር መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አጠቃላይ የኢትዮጵያ እና የፓኪስታን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሁሉም መስክ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን አምባሳደር ጀማል አብራርተዋል።
በየካቲት 2015 ዓ.ም ከ80 በላይ የፓኪስታን የንግድ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን መመልከታቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ እና የፓኪስታን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።