ቀጥታ፡

የቢል ኤንድ ሚልንዳ ጌትስ ፋዉንዴሽን በኢትዮጵያ ወረርሽኝን ለመቆጣጠርና በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላይ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 24/2015 (ኢዜአ) ፡- የቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ወረርሽኝን ለመቆጣጠርና በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላይ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

በቦትሰዋና ገቦሮኒ እየተካሄደ ካለዉ 73ኛው የአፍሪካ አህጉር የዓለም ጤና ድርጅት መድረክ ጎን ለጎን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ከቢል ኤንድ ሚልንዳ ጌትስ ፋዉንዴሽን ዓለም አቀፍ ልማት ፕሮግራም ዘርፍ ፕሬዝደንት ዶክተር ክርስቶፈር ኤልያስ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የፋዉንዴሽኑ ዓለም አቀፍ ልማት ፕሮግራም ዘርፍ ፕሬዝዳንት ዶክተር ክርስቶፈር ኤልያስ በኢትዮጵያ የእናቶችና ህጻናት ጤናን በማሻሻል ወረርሽኖችን ጨምሮ በሽታን መከላከልና መቆጣጠር ላይ እየተሰራ ያለዉ ስራ ዉጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል።



 

የክትባት አቅርቦትን በማሳደግ፣ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የሚሰራዉን የቅኝትና ቁጥጥር ስራ፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤና ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲሁም በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላይ የተያዘዉን ግብ ለማሳካት ድጋፋቸዉን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የክትባት አገልግሎትና የቤተሰብ ዕቅድን ተደራሽ በመድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንጻር ፋውንዴሽኑን ጨምሮ የአጋር ድርጅቶች ድርሻ ጉልህ መሆኑን አንስተው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አጽንኦት ሰጥተዋል።


 

ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ከአየር ንብረት ለዉጥና ሌሎች ተያያዠ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ እየተከሰቱ ያሉ እንደ ኮሌራ፣ ወባ በሽታ እና ሌሎች ወረርሽኖችን ለመቆጣጠር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በክትባት መከላከል የሚቻሉ እንደ ኮሌራ፣ ኩፍኝ፣ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር እና ፓልዮ በሽታን ለመከላከል ሚልንዳ ጌትስ እያደረገ ያለዉ ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑንም አክለዋል።

ዶክተር ደረጀ ወቅታዊነቱን የጠበቀ የክትባት ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻር ፋውንዴሽኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።

በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በቦትስዋና ገቦሮኒ እየተካሄደ በሚገኘው 73ኛው የአፍሪካ አህጉር የዓለም ጤና ድርጅት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም