ዓለም ወደ ዲጂታል አሰራር እየገባ በመሆኑ ሴት አመራሮች ይህንን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም ወደ ዲጂታል አሰራር እየገባ በመሆኑ ሴት አመራሮች ይህንን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 24/2015 (ኢዜአ) ፦ ዓለም ወደ ዲጂታል አሰራር እየገባ በመሆኑ ሴት አመራሮች ይህንን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት በማድረግ ራሳቸውንና ሀገራቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት አለባቸው ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ።
ዲጂታል ኢትዮጵያ እና የሴቶች ሚና በሚል ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተወጣጡ ሴት አመራሮች የተሳተፉበት መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩ የኢትዮጵያ የዲጂታል ጉዞ እና የሴቶች ሚና፣ በዲጂታል አለም ውስጥ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የዲጂታል ክፍፍል (digital divide) የሳይበር ትንኮሳና ጉልበተኝነትን (cyberbullying) መከላከል በሚሉት ላይ ያተኮረ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንደገለጹት ዓለም ወደ ዲጂታል አሰራር እየገባ በመሆኑ ሴት አመራሮች ይህንን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት በማድረግ ራሳቸውንና ሀገራቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለውን የዲጂታል ክፍፍል ለማጥበብ ሴት አመራሮች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የተናገሩት።
የዲጂታል ክፍፍል በፆታ፣ በዕድሜ፣ በአካባቢ እና በመጠቀሚያ መሳሪያዎች እንደሚስተዋል ገልጸው በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለውን የዲጂታል ክፍፍል ለማጥበብ ሴት አመራሮች ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራች ሲሆን በተለያየ ገፅታ የሚታይ የዲጂታል ክፍፍልን በማጥበብ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑም ተመላክቷል።