ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአለም በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙ ነዳጅ አምራች ካልሆኑ ሃገራት አንዷና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ነች-አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ

 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአለም በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙ ነዳጅ አምራች ካልሆኑ ሃገራት አንዷና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሆነች በባህሬን የኢፌዲሪ ቆንስል ጄኔራል  አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ ገለጹ።

አምባሳደር ሽፈራው በባህሬን ንጉሳዊ መንግስት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አብደላ አደል ፋኽሮ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው  በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ አብሮ ለመስራትና የንግዱን ማህበረሰብ ለማስተሳሰር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

አምባሳደሩ በውይይታቸው የሁለቱ ሃገራት የንግድ ግንኙነት በኮቪድ 19 ወቅት የተቋረጠውን መልሶ በማጠናከር ሁለቱም ሃገራት ተፈላጊ የሆኑ የንግድ ምርቶችን በመለየትና በተቋማት ትስስር ዙሪያ በመስራት ንግዱን ህጋዊ መሰረት በማስያዝ የንግድ ልውውጡን ማጎልበት በሚቻልበት ዙሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያና ባህሬን ካላቸው ቅርበት አንፃር የኢትዮጵያ ምርቶች እንደ ቡና፣ ሰሊጥና የቅባት አህሎች፣ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶች፣ ማዕድንና ቅመማ ቅመሞች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ እንስሳትና የሥጋ ውጤቶች ለባህሬን ገበያ ለማቅረብ የጋራ መግባቢያ ሠነድ ቢፈረም ሃገራቱን የጋራ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

መንግስት ለኢንቨስትመንት እንዲመች እንደ መንገድ፣ የትራንስፖርት፣ የኃይል አቅርቦትና ማበረታቻዎችን በማዘጋጀት፣ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ማድረጉንና የማምረቻና የኢንዱስትሪ ፖርኮችን በማልማት እየሰራ እንደሆነ አምባሳደሩ አብራርተዋል።

አቅም ያላቸው የባህሬን ባለሀብቶች በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በፋርማሲቲካል፣ በምግብ ማቀነባበሪያ፣ ጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ማዕድን ላይ ቢሳተፉ የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያጎለብት ተገልጿል።

ሚኒስትሩ በበኩላቸው ባህሬን ሁሉንም የፍጆታ ምርቶች ከውጭ ሀገር የምታስገባና መንግስታቸው በዋናነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት በባህሬን የንግድ ኤግዚቢሽን እንደሚካሄድ ገልጸው ኢትዮጵያን አንዷ የገበያ አማራጭ እንደሚያደርጉና በሁለቱ አገራት መካከል የንግድ ስምምነት እንዲኖር ለማድረግ ቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በባህሬን ትልቁ የኢንቨስትመንት ምንጭ Mumtalakat Holding የቦርድ አባል ሲሆኑ በቀጣይ በኢትዮጵያን በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የሚመለከታቸውን የቢዝነስ ማህበረሰብና ሃላፊዎች በማወያየትና በማበረታታት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሰሩ ለማድረግ እንደሚሰሩም አስረድተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም