ቀጥታ፡

በክህሎት ሥልጠና፣ የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸትና የንግድ ልማት ሥራዎች ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

 

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 23/2015 (ኢዜአ) ፡- የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በክህሎት ሥልጠና፣ የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸትና የንግድ ልማት ሥራዎች ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችል ስምምነት ሚልዮማንኒግ ከተሰኘ የስዊድን ኩባንያ ጋር ተፈራረመ።

ሥምምነቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሡ ጥላሁንና የሚልዮማንኒግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሊ ካሊል ፈርመውታል።

ሥምምነቱ በክህሎት ሥልጠና፣ የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸትና የንግድ ልማት ሥራዎች ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችል እንደሆነም ተጠቁሟል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሥምምነቱ ኢትዮጵያውያን ስዊድንን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

ሥምምነቱ ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች ተገቢው እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸውም ያስችላል ነው ያሉት።

በአገር ውስጥ የሚፈለገውን የሰው ኃይል በእውቀትና በክህሎት ለማዘጋጀት ሥምምነቱ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሕጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ሌላው የዓለም ክፍል የሚያደርጉትን የሥራ ሥምሪት ለማሳለጥ ሥምምነቱ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

አዳዲስ ክህሎቶችን ለማግኘት እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ የሚደረግ ጉዞን ለመቀነስም ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
 

የሚልዮማንኒግ ኩባንያ የኢትዮጵያ ዲቪዥን ኃላፊ ቢኒያም ፈቃዱ በበኩላቸው ኩባንያው ሥልጠናዎችንና የሥራ ዕድሎችን የሚያመቻች መሆኑን ተናግረዋል።

ኩባንያው የሥራ ዕድል አግኝተው በስዊዲንና በሌሎች የአውሮፓ አገራት የሚሰማሩ ዜጎች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅም እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለዜጎች በሚሰጠው የዕውቀትና ክህሎት ሥልጠናዎች በአገር ውስጥም ተወዳዳሪ ሆነው የሥራ ዕድል ማግኘት የሚያስችል መሆኑንም ነው ያስረዱት።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኩባንያው እንደሚሰራ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም