በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት ይሰራል - ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት ይሰራል - ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 23/2015 (ኢዜአ) ፡- በቀጣዩ ዓመት በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ገለጸች።
በሃንጋሪ፤ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለተሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን አቀባበል ተደርጎለታል።
ልዑኩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል።
አትሌቶች በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር ከሕዝቡ ጋር ደስታቸውን ተጋርተዋል።
በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በ2 ወርቅ፣ 4 ብርና 3 ነሃስ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችላለች።
ኢትዮጵያ በደረጃ ሰንጠርዥም ከአፍሪካ 2ኛ ከዓለም 6 ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በዚሁ ጊዜ እንደገለጸችው፤ በውድድሩ ኢትዮጵያዊያን በአንድነትና በመተባበር ጥሩ ውጤት አምጥተዋል።
በጥረታችሁ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረጋችሁ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች የአትሌቲክሱ ማኅበረሰብ ምስጋና ይገባቹሃል፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንም ምስጋና ያቀርባል ብላለች።
እ.አ.አ በ2024 በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት በልዩ ሁኔታ እንደሚሰራም ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ተናግራለች።
የአትሌቲክስ ልዑክ ቡድኑ መሪ አትሌት ገዛኸኝ አበራ በበኩሉ በውድድሩ ውጤታማ ለመሆን ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ድረስ ዝግጅት በማድረግ መሳተፍ መቻሉን ገልጿል።
"በውድድሩ ቆይታ ዘጠኝ ሜዳሊያ ይዘን መጥተናል፤ ውጤቱ የመጣው ከ 35 እስከ 37 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ባለው የአየር ጸባይ ነው" ያለው ቡድን መሪው ውጤቱ የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተጋድሎ የታየበት ነው ብሏል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው በውድድሩ አትሌቶቹ ያደረጉት ተጋድሎ የሚደነቅ ነው።
"የኢትዮጵያ ስም በእናንተ ተጠርቷል፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሕዝቦች ትኩረታቸውን ኢትዮጵያ ላይ እንዲሆን በማድረጋችሁ ኮርተንባችኋል" ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በየዘርፉ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት በትኩረት ሊሰራ ይገባል።
የአትሌቲክስ ማሰልጠኛዎችን ማጠናከር፣ መሮጫ መንገድ /ትራክ/ ያላቸውን ስታዲየሞችን መገንባትና የተደራጀ አትሌቲክስ ካምፕ ማዘጋጀት በአትሌቲክሱ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በስፋት ሊሰራባቸው እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት።
አትሌት ልዑል ገብረ ሥላሴ በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን ሩጫ ውድድር ለኢትዮጵያ የነሃስ ሜዳሊያ አስገኝቷል።
በቀጣይም ጠንክሮ በመስራት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመካስ ጥረት እንደሚያደርግም ነው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጠው አስተያየት የገለጸው።