በምዕራብና ቄለም ወለጋ ዞኖች ከ150 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የበቆሎ ሰብል እየለማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብና ቄለም ወለጋ ዞኖች ከ150 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የበቆሎ ሰብል እየለማ ነው
ግምቢ ፤ ነሐሴ 23/2015 (ኢዜአ)፡- በምዕራብና ቄለም ወለጋ ዞኖች ከ150 ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት የበቆሎ ሰብል እየለማ መሆኑን የየዞኖቹ ግብርና ጽሕፈት ቤቶች አስታወቁ።
ቄለም ወለጋ ዞን እና ምዕራብ ወለጋ ዞን በበቆሎ ምርት የሚታወቁ ዞኖች ከመሆናቸው በተጓዳኝ የዘንድሮው የዝናብ ሁኔታ ለሰብሉ አመች በመሆኑ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ታምኖ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፈይሳ ሃምቢሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2015/16 የምርት ዘመን በዞኑ በሰብል ከተሸፈነው 377 ሺህ ሔክታር አጠቃላይ መሬት ውስጥ 87 ሺሕ 820 ሄክታሩ በበቆሎ ሰብል የተሸፈነ ነው፡፡
በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች የበቆሎ ምርት በስፋት እንደሚመረት ተናግረው፤ የዞኑ አየር ሁኔታ ለበቆሎ ሰብል አመቺ እንደሆነና በእቅዱ ልክ ምርቱን ለማግኘት የሚያስችል እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በበቆሎ ከተሸፈነው መሬት ውስጥ አብዛኛው በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በመሆኑም የሚደረገውን የእንክብካቤ ስራ ቀላል እንዳደረገላቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የበቆሎ ምርታማነቱን ለመጨመርም ከ61 ሺሕ 701 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እና ከ2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ባለይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በዞኑ ጥቅም ላይ መዋሉን አስረድተዋል፡፡
በበቆሎ ሰብል ከተሸፈነው ማሳ ውስጥም 2 ሚሊዮን 931ሺሕ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን 63 ሺሕ 56 ሄክታር መሬት በበቆሎ ሰብል መሸፈኑን የገለጹት የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሙለታ ዋቅጅራ ናቸው፡፡
በበቆሎ ከተሸፈነው መሬት ውስጥም 56 ሺሕ 923 ሄክታሩ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ መሆኑን ገልጸው፤ ከአጠቃላዩ 2 ሚሊዮን 648 ሺሕ 352 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ መታቀዱን ገልጸዋል።
ለዚህም 23ሺህ 179 የአፈር ማዳበሪያና 4 ሚሊዮን 785 ሺህ 240 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል፡፡
በምርት ዘመኑ ከአንድ ሔክታር በአማካይ ከ35 ኩንታል በላይ ለማምረት ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡
በበቆሎ ልማቱ ተሳታፊ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል የዳሌ ሳዲ ወረዳ አርሶ አደር ያደሳ ሳሙኤል እንዳሉት በግብርና በለሙያ ምክር በመታገዝ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ ዘርተው እየተንከባከቡ ነው።
በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የዘሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ በዚህም ሙሉ የግብርና ቴክኖሎጂን መጠቀማቸውንና የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
በየዓመቱ በቆሎን በስፋት እንደሚያመርቱ የተናገሩት ደግሞ በምዕራብ ወለጋ ዞን የላሎ አሳቢ ወረዳ ታሲዮ ሞሌ ቀበሌ አርሶ አደር ተሰማ አለማየሁ ናቸው፡፡
በምርት ዘመኑ በአንድ ሔክታር ማሳ ላይ በቆሎ መዝራታቸውን ተናግረው፤ በባለሙያ ምክር በመታገዝ አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።