ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር አበክራ ትሰራለች - አምባሳደር አወል ወግሪስ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 23/2015 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር አበክራ እንደምትሰራ በናይጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አወል ወግሪስ ገለጹ።

አምባሳደር አወል ወግሪስ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ አቅርበዋል።

በዚህ ወቅት አምባሳደሩ ከናይጄሪያ ፕሬዚደንት ጋር በነበራቸው ውይይት የኢትዮጵያና የናይጄሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር በትጋት እንደሚሰሩ ለፕሬዝዳንቱ ገልጸውላቸዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል በተለያዩ መስኮች የተፈረሙ ስምምነቶችን ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚያስፈልግም አስታውሰዋል።

ለዜጎች ሕይወት መለወጥና ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ትስስር መጎልበት መስራት እንደሚገባም ነው አምባሳደር አወል ያመለከቱት።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው ጽንሰ ሀሳብ ችግሮች እንዲፈቱ እየሰራ ይገኛል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ በኢኮኖሚና በደህንነት ዘርፎች ያላትን ትብብር ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

አፍሪካውያን ለአፍሪካ እድገት መስራትና ውስጣዊ ችግሮቻችንን በጋራ መፍታት ይኖርብናል፤ ለዚህም በከፍተኛ ቁርጠኝነት መስራትና መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

እኛ አፍሪካውያን ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ማንም ሊያውቀን አይችልም ያሉት ፕሬዝዳንቱ አገር በቀል መፍትሔዎች ለሁሉም የሚበጅና ዘላቂነት ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ከ60 ዓመት በላይ ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም