ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና
በየሁለት ዓመቱ በዓለም አትሌቲክስ (በቀድሞ ስያሜው የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር) አዘጋጅነት የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከኦሊምፒክ ጨዋታና ከእግር ኳሱ የዓለም ዋንጫ ቀጥሎ፣ በግዝፈቱ የሚጠቀስ ስፖርታዊ ውድድር ነው።
ነገር ግን ሻምፒዮናው ከተጀመረበት ከእ.አ.አ 1983 እስከ 1991 ሲካሄድ የነበረው በየአራት ዓመቱ ሲሆን በጃፓን ቶኪዮ እ.አ.አ በ1991 ከተካሄደው ሶስተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ ውድድሩ በየሁለት ዓመቱ እንዲካሄድ መደረጉን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል።
ሻምፒዮናው ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ1983 በፊንላንድ ሄልሲንኪ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በሻምፒዮናው ላይ ከ153 አገራት የተወጣጡ ከ1 ሺህ 300 በላይ አትሌቶች ተሳትፈውበታል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከናወን ኢትዮጵያ በ10 አትሌቶች በ3000 ሜትር መሰናከል፣ 5000 ሜትር፣ 10000 ሜትር፣ ማራቶንና 20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድሮች ተሳትፋለች።
ከተሳተፉት አትሌቶች መካከል ከበደ ባልቻ በማራቶን ተወዳድሮ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ በሻምፒዮናው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ ማስገኘት የቻለ ሲሆን አፍሪካ በሻምፒዮናው ያገኘችው የመጀመሪያ ሜዳሊያ ሆኖ ተመዝግቧል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው 15ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1987 በጣልያን ሮም ከተካሄደው ሁለተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አልተሳተፈችም።
3ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በጃፓን ቶኪዮ ኦሊምፒክ ስታዲየም እ.አ.አ በ1991 የተካሄደ ሲሆን በውድድሩ ላይ ከ167 አገራት የተውጣጡ 1 ሺህ 517 አትሌቶች ተሳትፈዋል።
በዚህ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በአትሌት ፊጣ ባይሳ አማካኝነት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች፡፡
እ.አ.አ 1993 አራተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በጀርመን ስቱትጋርት የተካሄደበት ዓመት ነው።
በሻምፒዮናው በ10 ሺህ ሜትር የመጀመሪያው ወርቅና በ5 ሺህ ሜትር ውድድር ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ በሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አማካኝነት ማግኘት ተችሏል።
እንደዚሁም አትሌት ፊጣ ባይሳ ደግሞ ሌላ ነሐስ አክሎ ኢትዮጵያ ሶስት ሜዳሊያ አግኝታለች።
እ.አ.አ በ1995 ጉተንበርግ ስዊድን በተካሄደው አምስተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ በአትሌት ደራርቱ ቱሉ ደግሞ ብር የተገኘበት ሻምፒዮና ነበር፡፡
እ.አ.አ በ1997 ስድስተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በግሪክ አቴንስ ግሪክ ሲካሄድ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በ10 ሜትር ከፖል ቴርጋት ጋር ተናንቆ ወርቅ የተገኘበት ክስተት የሚዘነጋ አይደለም።
ሰባተኛው ሻምፒዮና በስፔን ሲቪል ኢስታዲዮ ኦሊምፒኮ ዴ ላ ካርቱጃ ስታዲየም እ.አ.አ በ1999 ሲከናወን ልማደኛው ኃይሌ ገብረስላሴ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ አሰፋ መዘገቡ ደግሞ ነሐስ ሜዳሊያ አስገኝተዋል።
አትሌት ጌጤ ዋሜ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት በሻምፒዮናው ታሪክ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሴት አትሌት መሆን ችላለች።
አትሌት አየለች ወርቁ በ5 ሺህ እንዲሁም አትሌት ቁጥሬ ዱለቻ በ1 ሺህ 500 በተመሳሳይ የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በድምሩ 5 ሜዳሊያ በማግኘት ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ ውድድሩን አጠናቃለች።
እ.አ.አ በ2001 በካናዳ ኤድመንተን ስምንተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካሄደ ሲሆን በወንዶች ማራቶን አትሌት ገዛኸኝ አበራ በማሸነፍ በሻምፒዮናው ታሪክ በርቀቱ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘት ችሏል።
አትሌት አሰፋ መዝገቡ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የብር፣ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች ሚሊዮን ወልዴ የብር እና አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የነሐስ ሜዳሊያ ለአገራቸው አስገኝተዋል።
በሴቶች የ10 ሺህ ሜትር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ብርሃኔ አደሬ እና ጌጤ ዋሚ ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት አረንጓዴው ጎርፍ በኤድመንተን እንዲደምቅ አድርገዋል።
አትሌት አየለች ወርቁ በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች የነሐስ ሜዳሊያ ለአገሯ አምጥታለች።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በአጠቃላይ 8 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም 7ኛ ደረጃ ይዛ በሻምፒዮናው ተሳትፎዋ የተሻለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች።
እ.አ.አ. በ2003 በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው ዘጠነኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች በ10 ሺህ ሜትር አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና በስለሺ ስህን ከአንደ እስከ ሶስት ተከታትለው በመግባት የኢትዮጵያን የበላይነት ያረጋገጠ ድል አስመዝግበዋል።
አትሌት ቀነኒሳ በ5 ሺህ ሜትር ወርቅ በማግኘት የድርብ ድል ባለቤት የሆነበት ታሪካዊ ውድድርም ነበር።
በሴቶች 10 ሺህ ሜትር አትሌት ብርሃኔ አደሬና ወርቅነሽ ኪዳኔ ወርቅና ብር ማግኘት የቻሉ ሲሆን ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በ5 ሺህ ሜትር ወርቅ አግኝታለች።
10ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካሄደው የመጀመሪያ ሻምፒዮና በተካሄደበት ፊንላንድ ሄልሲንኪ እ.አ.አ በ2005 ነው።
በሻምፒዮናው በ10 ሺህ ሜትር አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ወርቅ፤ አትሌት ስለሺ ስህን የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።
በ5 ሺህ ሜትር አትሌት ስለሺ ስህን የብር ሜዳሊያ አምጥቷል።
በሴቶች በ5 ሺህ ሜትር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋርና እጅጋየሁ ዲባባ ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት ኢትዮጵያን አኩርተዋል።
በተመሳሳይ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ ብርሃኔ አደሬና እጅግአየሁ ዲባባ ከ1ኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው እንድትደምቅ አድርገዋታል።
ጥሩነሽ ዲባባ በ5 ሺህና በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ በማግኘት እንዲሁም እጅጋየሁ ዲባባ በተመሳሳይ ሁኔታ በ10 ሺህ እና በ5 ሺህ ርቀት በአንድ ውድድር ላይ ነሐስ በማምጣት በታሪክ የመጀመሪያዎቹ እህትማማቾች መሆን ችለዋል።
11ኛው ሻምፒዮና እ.አ.አ በ2007 በጃፓን ኦሳካ ናጋይ ስታዲየም ሲካሄድ አትሌት ቀነኒሳ በቀለና አትሌት ስለሺ ስህን በ10 ሺህ ሜትር የወርቅና ብር እንደዚሁም ጥሩነሽ ዲባባ ከሆድ ሕመሟ ጋር ታግላ በ10 ሺህ ሜትር ለሀገሯ ወርቅ መምጣት የቻለች ሲሆን በመሰረት ደፋር ደግሞ በ5 ሺህ ወርቅ ለማግኘት ተችሏል።
ኢትዮጵያ በ4 ሜዳሊያ ከአለም 4ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
እ.አ.አ በ2009 በጀርመን በርሊን በተከናወነው 12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በተለያዩ ርቀቶች የሚሳተፉ 38 አትሌቶችን ይዛ ቀርባለች፤ ቡድኑ በመካከለኛ ርቀት ጭምር የሚሳተፉ አትሌቶችን ያቀፈ ነበር።
በሻምፒዮናው በወንዶች 5 ሺ ሜትርና 10 ሺ ሜትር ቀነኒሳ በቀለ ሁለት ወርቅ በማምጣት አዲስ ታሪክ የጻፈበት ክስተት ነበር።
በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ደረሰ መኮንን የብር ሜዳልያን ሲያሳካ፣ ፀጋዬ ከበደ በማራቶን ሁለተኛውን የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።
በሴቶች በመሰረት ደፋር በ5000 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ፣ መሰለች መልካሙ በ10 ሺህ ሜትር የብር እና ውዴ አያሌው የነሐስ፣ እንዲሁም አሰለፈች መርጊያ በማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝተዋል።
ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ስምንት ሜዳሊያ በመሰብሰብ ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ሆኖ አልፏል።
እ.አ.አ በ2011 በኮሪያ ሪፐብሊክ ዴጉ ላይ በተካሄደው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካፈለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን 34 አትሌቶች የተካከቱበት ነበር።
በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ኢብራሂም ጄይላን በመጨረሻው ዙር ፍጥነቱን በመጨመርና አስደናቂ የአጨራረስ ብቃቱን በመጠቀም ከኋላ ተነስቶ እንግሊዛዊውን አትሌት ሞ ፋራን ያሸነፈበት መንገድ አድናቆት ያስቸረውና ኢትዮጵያውያንን በደስታ ያስፈነጠዘ ነበር።
በሻምፒዮናው አትሌት ደጀን ገብረ መስቀል በ5000 ሜትር፣ ኢማና መርጊያ በ10 ሺህ ሜትር፣ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በማራቶን እንዲሁም መሰረት ደፋር በ5000 ሜትር አራት የነሐስ ሜዳሊያዎች አስገኝተዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው አምስት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ 10ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
እ.አ.አ በ2013 በሩሲያ ሞስኮ በተካሄደው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በመሰረት ደፋር በ5000 ሜትር ወርቅ፣ በጥሩነሽ ዲባባ 10 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ በ800 ሜትር ወንዶች በመሐመድ አማን ወርቅ ማምጣት ተችሏል።
በሌሎች ርቀቶች ሶስት የብርና ሶስት የነሐስ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ኢትዮጵያ ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች።
እ.አ.አ በ2015 በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ገንዘቤ ዲባባ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወርቅ ማምጣት ችላ ነበር።
በቤጂንጉ የዓለም ሻምፒዮና አትሌት አልማዝ አያና በ5000 ሜትር ወርቅና ማሬ ዲባባ በማራቶን ወርቅ ያገኙ ሲሆን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በአምስት ሜዳሊያዎች ከዓለም አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡
በ2017 በ16ኛው የለንደን ዓለም ሻምፒዮን አምስት ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያ በማግኘት በዓለም ሰባተኛ ደረጃን ይዛ ተመልሳለች።
ከሜዳሊያዎቹ ውስጥም በ5 ሺህ ሜትር በሙክታር እድሪስና በ10 ሺህ በአልማዝ አያና ሁለት የወርቅ ሜዳልያ ማግኘት ተችሏል፡፡
በ2019 የተካሄደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኳታር ዶሃ የተደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ በሁለት ወርቅና በአራት ብር በአጠቃላይ ስድስት ሜዳሊያዎች ማምጣት ችላለች።
አትሌት ሙክታር እድሪስ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች በማሸነፍ በተከታታይ ሁለት ሻምፒዮናዎች በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ችሏል።
በማራቶን ደግሞ አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።
በሻምፒዮናው አትሌት ለሜቻ ግርማ በ3000 መሰናክል የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
ከዚያ በኋላ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሻምፒዮናው ለሁለት ዓመታት ሳይካሄድ ቆይቷል።
እ.አ.አ. በ2022 ዓለም ከወረርሽኑ አገግማ በአሜሪካ ኦሬጎን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ስኬታማውን የዓለም ሻምፒዮና ያገኘበት ውጤት አስመዘገበ።
በሻምፒዮናው አትሌት ለተሰንበት ግደይ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች፣ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በ5ሺህ ሜትር ሴቶች፣ አትሌት ጎይቲቶም ገብረስላሴ በሴቶች ማራቶን እና አትሌት ታምራት ቶላ በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ኢትዮጵያን ያኮራ ድል አስመዘገቡ።
አትሌት ጉዳፍ በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የብር ሜዳሊያ በማግኘት በሻምፒዮናው ሁለት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማራቶን በሁለቱም ጾታ የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን ማሻሻል የቻሉ ሲሆን አትሌት ለተሰንበት በ10 ሺህ ሜትር የዓመቱን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች።
ኢትዮጵያ በኦሬገኑ ዓለም ሻምፒዮን ከአራቱ ወርቅ በተጨማሪ አራት የብርና ሁለት የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን በማግኘት ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ አጠናቃለች።
የኦሬገኑ ውድድር ኢትዮጵያ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችበት ውድድርም ሆኖ አልፏል።
ደማቅ ስኬት ላስመዘገበው የአትሌቲክስ ቡድን በአዲስ አበባ ደማቅ የጀግና አቀባበል የተደረገለት ሲሆን አትሌቶቹ በመዲናዋ አውራ ጎዳናዎች በመዘዋወር ከሕዝቡ ደስታውን በመግለጽ ድላቸውን አክብረዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት እ.አ.አ ከነሐሴ 19 እስከ 27 ቀን 2023 በሀንጋሪ ቡዳፔስት ናሽናል አትሌቲክስ ሴንተር ስታዲየም በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ2 የወርቅ፣4 የብር እና በ3 የነሐስ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም ስድስተኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በ34 አትሌቶች የተወከለች ሲሆን በሻምፒዮናው በ1 ሺህ 500፣ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል፣ በ5 ሺህ ሜትር፣ በ10 ሺህ ሜትርና በማራቶን በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ800 ሜትር በሴት ብቻ ተሳትፋለች።
ኬንያ በ3 የወርቅ፣ በ3 የብር እና በ4 ነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም አምስተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዛለች።
አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ስፔንና ጃማይካ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በሻምፒዮናው መክፈቻ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች ፍጻሜ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ፣ አትሌት ለተሰንበት ግደይና አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት ያስመዘገቡት ድል ተጠቃሽ ነው።
በሴቶች ማራቶን በአስገራሚ የቡድን ስራ አትሌት አማኔ በሪሶና አትሌት ጎይቲቶም ገብረስላሴ ያስገኙት የወርቅና የብር ሜዳሊያ የሚረሳ አይደለም።
በሻምፒዮናው የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማለዳውን አዲስ አበባ ሲገባ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን በመዲናዋ አውራ ጎዳናዎች ከሕዝቡ ጋር በመሆን ደስታውን ተካፍሏል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1985 በጣልያን ሮም ከተካሄደው ሁለተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በስተቀር በተሳተፈችባቸው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 35 የወርቅ፣ 38 የብር እና 31 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት በድምሩ 104 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሻምፒዮናው የምንጊዜም የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እ.አ.አ በ2025 በጃፓን ቶኪዮ ይካሄዳል።