ቀጥታ፡

በአንድነትና በመተባበር ስንሰራ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን የአትሌቶቻችን ድል አድራጊነት ለሌላውም አስተማሪ ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2015 (ኢዜአ)፦ በአንድነትና በመተባበር ስንሰራ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን የአትሌቶቻችን ድል አድራጊነት ለሌላውም አስተማሪ ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሀንጋሪ ቡዳፔስት ከተማ የተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን እና የኢትዮጵያዊያን አትሌቶችን ስኬት አስመልክቶ ያስተላለፈው መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

በአንድነትና በመተባበር ስነሰራ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን የአትሌቶቻችን ድል አድራጊነት ለሌላውም አስተማሪ ነው፡፡

በሀንጋሪ ቡዳፔስት ከተማ የተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ እንደወትሮው ሁሉ ከፍ ብሎ የተውለበለበበት መድረክ ነበር፡፡ ከድሉ ባሻገር የነበረው የቡድን ሥራ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ያኮራ ነበር፡፡

“አረንጓዴው ጎርፍ” እየተባለ የሚጠራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን፤ ዘንድሮም ስያሜውን በሚመጥን መልኩ አትሌቶቻችን ተከታትለው በመግባት የሀገራችንን የድል ታሪክ ደግመዋል፡፡

በተለይ ሴቶች አስር ሺህ ሜትርና በማራቶን ሩጫ የታየው የቡደን ሥራ፣ እርስ በእርስ መናበብ እና መረዳዳት ከድል ምክንያትነቱ ባሻገር ኢትዮጵያዊያን ስንተባበር ተአምር መሥራት እንደምንችል አመላካች ነበር፡፡

አትሌቶቻችን በሩጫ ወቅት መረጃ በመለዋወጥ፣ በመተጋገዝ እና አንዳቸው ሌላውን በመጠበቅ እስከ መጨረሻው ድረስ በቡድን ተጉዘዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ በሩጫ ላይ አትሌቶቿ ባሳዩት መተባበርና መተጋገዝ ተምሳሌት መሆኗን ዳግም ያሳየ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል፡፡

ሀገራችን በጠቅላላ ውድድሩ ሁለት የወርቅ፣ አራት የብር እና ሦስት የነሀስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ስድስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ሆና ውድድሩን አጠናቅቃለች፡፡

ጥሩ ውጤት ያስመዘገብንባቸዉም ሆነ በተሳተፍንባቸው ውድድሮች በቀጣይ ዓመት ለሚደረገው የኦሎምፒክ ውድድር ስንቅ የሚሆኑ ተሞክሮዎች ተገኝተዋል፡፡

በዋናነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአትሌቲክስ ውድድሮች ጠፍቶ የነበረው የኢትዮጵያዊያን የቡድን ሥራ በዘንድሮው ውድድር በጉልህ መታየቱ በዘርፉ ያለንን ስኬት በቀጣይ ጊዜያት ለማሻሻል የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል፡፡

ከምንም በላይ ከውጤቱ ባሻገር ውጤቱ የተገኘበት መንገድ ኢትዮጵያዊያንን በጋራ ያስደሰተ፤ የሀገራዊ አንድነታችን ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ አኩሪ ድል ነው፡፡

ሀገርን በተለያዩ ዓለምአቀፍ መድረኮች በመወከል ድል ማስመዝገብ የሚወደስ ተግባር ነው፡፡ ሀገራችን ከጊዜያዊ አሉታዊ ፈተናዎች ባሻገር በተለያዩ ዘርፎች ድል የሚያደርጉ የትጉሀን ሀገር መሆኗን ለዓለም ማሳየት በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ በጥረታቸው ድል የሚያደርጉ፣ የሀገራቸውን መልካም ገፅታ አጉልተው የሚሳዩ የብርቅዬ ልጆች ቤት መሆኗ ዛሬም በዓለም አደባባይ ታይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከፈተናዋ በላይ ተስፋዋ የለመለመ፣ አዎንታዊ ስኬቷም በእጅጉ እንደሚልቅ በተለያዩ ዘርፎች እየታየ ነው፡፡

በስፖርት ዘርፉ ከትውልድ ወደ ትውልድ የቀጠለው የአሸናፊነት ገድል በቀጣይ ጊዜያትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እንደተለመደው በትብብር መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየዘርፉ ድል ማድረጓን ትቀጥላለች!

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም