በከተማ የአረንጓዴ ልማት ላይ በስፋት እየተሰራ ነው... የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
በከተማ የአረንጓዴ ልማት ላይ በስፋት እየተሰራ ነው... የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 23/2015 (ኢዜአ) ፡- በከተማ የአረንጓዴ ልማት ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የመበደር ብቃት እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ ከተሞችን መገንባት በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከፓሪስ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ዳይሬክተር ጋር ተወያይተዋል።
በሚኒስትሯ የተመራ ልዑክ ከፓሪስ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ዳይሬክተር፣ የከተሞች የአየር ንበረት ኃላፊ እና የስነ-ምህዳር እና የአየር ንብረት ለውጥ ዲፓርትመንት ኃላፊ ጋር ስለ ከተሞች የመበደር ብቃት እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ ከተሞችን ስለመገንባት ውይይት አድረገዋል፡፡
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት በከተማ የአረንጓዴ መሰረተ ልማት ላይ በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ሚኒስትሯ ማብራራታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በተያያዘም የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ ተቋማዊ እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መርሃ ግብሮችን በመንደፍ እንዲሁም በከተሞች የሚስተዋለውን ድህነት ለመቅረፍ የስራ እድል በመፍጠርና እና የከተማውን ማህበረስብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየሠራ እንደሆነም ገለጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ ሀገር በቀል እና አለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሀገሪቱ ያሉትን ከተሞች የገንዘብ እና ተቋማዊ አቅም ለማሳደግ ያለመ የከተማ አቀፍ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡