በቀጣዩ ዓመት በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት ይሰራል -ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣዩ ዓመት በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት ይሰራል -ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 23/2015(ኢዜአ)፦ በቀጣዩ ዓመት በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ገለጸች።
በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለተሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን አቀባበል ተደርጎለታል።
ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ በዚሁ ወቅት እንዳለችው በውድድሩ ኢትዮጵያዊያን በአንድነትና በመተባበር ጥሩ ውጤት አምጥተዋል።
በጥረታችሁ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረጋችሁ አትሌቶች ምስጋና ይገባቹሃል፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንም ምስጋና ያቀርባል ብላለች።
እ.አ.አ በ2024 በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት በልዩ ሁኔታ እንደሚሰራም ነው የተናገረችው።
የልዑካን ቡድኑ መሪ አትሌት ገዛኸኝ አበራ በውድድሩ ውጤታማ ለመሆን ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ድረስ ዝግጅት በማድረግ ለመሳተፍ መቻሉን ገልጿል።
'በውድድሩ ቆይታ ዘጠኝ ሜዳሊያ ይዘን መጥተናል ፤ውጤቱ የመጣው ከ35 እስከ 37 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ላይ ተወዳድረን ነው' ሲልም ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በየዘርፉ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እየተሰራ ነው።
ከዚህ ውስጥም ማሰልጠኛዎችን ማጠናከርና የተደራጀ አትሌቲክስ ካምፕ ማዘጋጀት ዋነኞቹ እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንዳሉት በውድድሩ አትሌቶቹ ያደረጉት ተጋድሎ የሚደነቅ ነው።
'የኢትዮጵያ ስም በእናንተ ተጠርቷል በዓለም ዙሪያ ያሉ ሕዝቦች ትኩረታቸውን ኢትዮጵያ ላይ እንዲሆን በማድረጋችሁ ኮርተንባችኋል' ብለዋል።
33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እ.አ.አ ከሐምሌ 26 እስከ ነሐሴ 11 /2024 በፓሪስ እንደሚካሄድ ከዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።