ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል- የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2015 (ኢዜአ)፡- በመዲናዋ የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ስራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

የባለስልጣኑ የተጠናቀቀው በጀት አመት እቅድ አፈጻጸምና በ2016 እቅድ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ተብሏል።

የባለስልጣኑ የእቅድ፣ዝግጅት፣ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ አሊ፤ በ2015 በጀት ዓመት በከተማዋ የሚካሄዱ ማንኛውም ግንባታዎች የሕንጻ አዋጁን የተከተሉ እንዲሆኑ ክትትልና ቁጥጥር ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

የክትትልና ቁጥጥር ተግባሩ በተያዘው በጀት ዓመትም አሰራርን ከማዘመን ስራ ጋር በትኩረት የሚከናወን መሆኑን አረጋግጠዋል።

በበጀት ዓመቱ በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለመቀነስ፤ የግንባታ እንቅስቃሴው ሕግና ስርአትን የተከተለ እንዲሆን፤ የከተማዋ  መዋቅራዊ ፕላን የሕንጻ አዋጁን መሰረት አድርጎ እንዲካሄድም ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በተጨማሪም የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ ለመፍታት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተጀመሩ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።

ከ2015 በጀት ዓመት ከ134 ሺህ በላይ ሕገ- ወጥ ማስታወቂያዎች ከደረጃ በታች በመሆናቸው ምክንያት እንዲነሱ መደረጉንም አቶ ሞገስ ገልጸዋል።

ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተገልጋዮች ደግሞ በዘርፉ የተቀመጠውን የጥራት ደረጃን በማሟላታቸው የማስታወቂያ ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ29 ሺህ በላይ አልሚዎች በአዲሱ የሕንጻ ቀለም ስታንዳርድ መሰረት የፕላን ስምምነት መውሰዳቸውንም ነው ያስረዱት።

የሚከናወኑት ግንባታዎች ከልማት ፋይዳቸው ባሻገር የከተማዋን ውበት የሚጨምሩ፣ ማራኪና ዘመናዊ እንዲሆኑም ሰፋፊ ስራዎች መከናወቸውንም እንዲሁ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በቅርቡ የተሾሙት ኢንጅነር አውራሪስ ከበደ፤ የተጀመሩ መልካም ስራዎችና ተሞክሮዎችን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም