ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በደቡብ -ደቡብ ትብብር ለፍትሐዊና አካታች የዓለም ስርዓት ግንባታ ሂደት የሚኖራትን ሚና የሚያጠናክር ነው- አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 22/2015 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በደቡብ-ደቡብ ትብብር ለፍትሐዊና አካታች የዓለም ስርዓት መገንባት የሚኖራትን ሚና የሚያጠናክር መሆኑን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ ጥምረቱን እንድትቀላቀል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች ብስለት የተሞላበት የዲፕሎማሲ ጥረት አድርገዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ ጉባኤ በይፋ አባል መሆኗ ይታወቃል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በታላቅ ስኬት የሚጠቀስ የዲፕሎማሲ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚቻልባቸው ዲፕሎማሲያዊ መድረኮችን በአግባቡ ለመጠቀም ሰፊ ስራ መሰራቱን በመጥቀስ፤ የብሪክስ አባል እንድትሆን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ መደረጉን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ኢትዮጵያ ነጻነቷን ያስጠበቀች፣ ለተገፉ ሀገራት ድምፅ የሆነች፣ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መመስረት ሰፊ ሚና የተጫወተች ሀገር መሆኗን ለአባል ሀገራት መሪዎች በተናጥልና በጋራ መድረኮች ማስገንዘባቸውን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ውስጥ መሆኗን በመግለፅ የደቡብ - ደቡብ ትብብርን ለማጠናከር ይህችን ታላቅ ሀገር ማካተት እንደሚገባ በአፅንኦት በማስረዳትና በማሳመን ጥያቄው ተቀባይነት እንዲኖረው አድርገዋል ነው ያሉት።

በዚህም የአባልነት ጥያቄ ካቀረቡ 40 አገራት መካከል ተቀባይነት ካገኙ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች ብለዋል።

የደቡብ-ደቡብ የትብብር መድረክ ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነትን መርሁ ያደረገ መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ሙክታር፤ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏም የትብብር መድረኩ ተጠቃሚ ያደርጋታል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን በደቡብ-ደቡብ ትብብር ለፍትሐዊና አካታች የዓለም ስርዓት መገንባት የሚኖራትን ሚና የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።

ጥምረቱ አባል ሀገራቱ የፖሊሲ ነጻነታቸውን በጠበቀና በትብብር ጥቅሞቻቸውን የሚያስጠብቁበትን አማራጭ ያሰፋልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ በፋይናንስና የኢንቨስትመንት የትብብር መስኮች ሰፊ ዕድል እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለጀመረቻቸው የልማት ስራዎች መሳካት ተጨማሪ የፋይናንስ አቅም እንድታገኝ፣ ወደ ውጭ ለምትልካቸው ምርቶችም ሰፊ የገበያ አማራጭ የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።

አባል ሀገራቱ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ሰፊ ልምድ ያላቸው መሆኑም ለኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ሽግግር መሳካት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጂኦ- ፖለቲካዊ ተፅዕኖዋ፣ ከህዝብ ብዛቷ፣ ከመልማት አቅሟና በዓለም አቀፍ መድረኮች ካላት ተደማጭነት አንጻር፣ በትብብር ለመስራት በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሀገር እንደሆነችም አብራርተዋል።

ለረጅም ዓመታት የአፍሪካ ድምፅ የሆነችው ኢትዮጵያ ጥምረቱን መቀላቀሏ ብዙ ትርጉም አለው ያሉት አምባሳደር ሙክታር፤ በተለይም ለታዳጊ ሀገራት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት የግዛት አንድነት መከበር፣ ለጋራ ጥቅም በመተባበር ላይ ያላት ፅኑ አቋም ከጥምረቱ አባል ሀገራት ጋር አካታችና ፍትሐዊ የዓለም ስርዓት እንዲገነባ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያጠናከር ጠቁመዋል።

በብሪክስ 15ኛ ጉባኤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ አርጀንቲናና ግብፅ ጥምረቱን እንዲቀላቀሉ መወሰኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም