ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ተቋርጦ የነበረውን የዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለማስቀጠል ስምምነት ላይ ደረሰ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ተቋርጦ የነበረውን የዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለማስቀጠል ስምምነት ላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡

በፈረንጆቹ 2020 በኢትዮጵያ በፀጥታ ችግርና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለማስቀጠል ነው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመነጋገር ስምምነት ላይ የተደረሰው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከተመድ ተወካዮች ጋር በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አፈፃፀምና ሥምሪት ላይ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።

በስምምነቱ መሠረት ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ለማስቀጠል በፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የቅድመ ስምሪት ስልጠና የወሰዱ የፖሊስ መኮንኖችን ብቃት ለመመዘን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ስለ መጠናቀቁም ከፌዴራል ፖሊስ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ እንዲሁም ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የተውጣጡ የፖሊስ መኮንኖች የዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ምዘና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም