ግብርናን ለማዘመን በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ግብርናን ለማዘመን በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 22/2015 (ኢዜአ) ፦ግብርናን ለማዘመን በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከግሪን አግሮ ሶሎሽንስ ሀላፊነቱ ከተወሰነ የግል ማህበር ጋር የግብርና መረጃዎችን ዲጂታላይዝ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ እና የግሪን አግሮ ሶሎሽንስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አብርሃም እንድሪያስ ተፈራረመዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት በመንግስትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ግብርናን ለማሻሻል ተቋሙ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው።
የተለያዩ መተግበሪያዎችን በማልማት ተደራሽ ማድረግ፣ የተሰበሰበውን መረጃ በአንድ ቋት መያዝ እና የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ላይ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግስትና በግል ባለሃብቶች የተጀመረውን ግብርናውን የማዘመን ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ይህን ለማጠናከር ኢንስቲትዩቱ ዛሬ መፈራረሙን ገልጸው፤ አርሶአደሩ በቀላሉ መረጃዎችን በማግኘት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል።
በዚህም በዘመናዊ መንገድ የግብርና መረጃዎችን መሰነድ፣ ማስተላለፍ እንዲሁም ለአርሶ አደሩ የገበያ መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ስራዎችን ይሰራል ብለዋል።
በስምምነቱ መሰረት የአየርንብረት፣ የአፈር ማዳበሪያና የዋና ዋና ሰብሎችንና የአትክልትና ፍራፍሬ መረጃዎችን ዲጂታላይዝ ይደረጋሉ ብለዋል።
በተጨማሪም ስምምነቱ አነስተኛ የእርሻ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል ሲሆን፤ ለሶስት ዓመታት የሚቆይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ስምምነቱ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ትግራይ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 150 ወረዳዎች በተለይ በኩታ ገጠም በሚያመርቱ አካባቢዎች ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
በዚህም የሚለሙ መተግበሪያዎችን ለአርሶአደሩ ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዙ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አብርሃም እንድሪያስ በበኩላቸው የግብርና መረጃዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ስራዎች ላይ 1 ሚሊየን 50 ሺህ አርሶደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
የግብርና መረጃዎችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በሚሰራው ስራ ተጠቃሚ ለሚሆኑ 82 ሺህ ወጣቶች ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።
በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በሶማሊኛ እና በሲዳምኛ ቋንቋዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ይሆናል ብለዋል።
መረጃው በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የነጻ ስልክ መስመር 8028 አገልግሎትን፣ በ''ለእርሻ ዲጂታል መተግበሪያ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽ ይሆናሉ።
ከዚህ በፊት ለአርሶ አደሩ በነጻ ስልክ መስመር በ8028 አጠቃላይ መረጃ፣ በ6077 የገበያ መረጃ እንዲሁም በኢ-ቮቸር ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም መረጃ ሲሰጥ መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።