ከሚሌ ኳራንቲን 7 ሺህ በጎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማጓጓዝ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ከሚሌ ኳራንቲን 7 ሺህ በጎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማጓጓዝ ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2015(ኢዜአ)፦ከሚሌ ኳራንቲን 7 ሺህ በጎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማጓጓዝ መጀመሩን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ገለጸ።
ቀደም ሲል በጎች በጂቡቲ ኳራንቲን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ይላኩ እንደነበር ይታወሳል።
በመስኩ የሚስተዋሉ የጤና ምርመራ፣ የማቆያና ወቅቱን ጠብቆ የመላክ ችግሮችን ለመፍታት በአፋር ክልል የሚሌ ኳራንቲን ማዕከል መገንባቱ ይታወቃል።
ይህ የሚሌ ኳራንቲን በሳዑዲ አረቢያ እውቅና ያገኘ ሲሆን በጅቡቲ ዶራሌ ወደብ በኩል በጎችን በቀጥታ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መላክ ተጀምሯል።
በቀጣይም የሚሌ ኳራንቲን በመካከለኛው ምስራቅና ሌሎች አገራት እውቅና እንዲያገኝ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ ለኢዜአ እንደተናገሩት የሚሌ ኳራንቲን ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ 7 ሺህ በጎች በየብስ ትራንስፖርት ወደ ጂቡቲ ወደብ መጓጓዛቸውን ጠቁመው ከወደቡም በመርከብ በመጫን ወደ ሳኡዲ አረቢያ መላክ መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የአገሪቷን የወጪ ንግድ ለማሳለጥ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።