የኢትዮጵያ ገንቢ ገለልተኛ የዲፕሎማሲ መርህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነትና አመኔታን አትርፎላታል - አንጋፋ ዲፕሎማቶች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ገንቢ ገለልተኛ የዲፕሎማሲ መርህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነትና አመኔታን አትርፎላታል - አንጋፋ ዲፕሎማቶች
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 22/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ገንቢ ገለልተኛ የዲፕሎማሲ መርህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነትና አመኔታን ያተረፈላት መሆኑን የኢትዮጵያ የቀድሞ አንጋፋ ዲፕሎማቶች ተናገሩ።
የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ጥረትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን እንቅስቃሴ በማስመልከት ኢዜአ የቀድሞውን አንጋፋ ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና እና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑትን ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉን አነጋግሯል።
የቀድሞ አምባሳደሮቹ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ የገለልተኛ አቋም ዲፕሎማሲ መስራች መሆኗን ጠቅሰው ይህም ከአገራት ጋር በትብብር ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለመከተሏ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደር ጥሩነህ በማብራሪያቸው፤ የገለልተኛ አቋም ዲፕሎማሲ እ.ኤ.አ በ1945 የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ወቅት ዓለም በምስራቅና ምዕራብ ጎራ ለሁለት በተከፈለበት ወቅት የተፈጠረ መሆኑን አስታውሰዋል።
በወቅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ታላላቅ ከሚባሉት አገራት ህንድ እና ኢንዶኔዥያ ከሁለቱም ጎራ ሳንቀላቀል የራሳችን አቋም አለን በሚል የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄን መመስረታቸውንም ያስረዳሉ፡፡
ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የዓለም ወደ አንድነት መምጣት ንቅናቄውን አዳክሞት ነበር ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፤ በኃያላን አገራት መካከል የተጀመረው ፍጥጫ ዳግም ገለልተኛ ሀገራት ጎልተው እንዲወጡ አድርጓል ብለዋል፡፡
ገለልተኛ ማለት አቋም የሌለው ማለት አይደለም የሚሉት አምባሳደር ጥሩነህ፤ ከየትኛውም ጎራ ያልወገነ የራሴን መብትና ጥቅም ያስከብርልኛል ያሉትን አቋም በነፃነት የማራመድ እሳቤ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚሁ የዲፕሎማሲ መርህ እየተንቀሳቀሰች ያለችው ኢትዮጵያ የምትከተለው የ ገንቢ ገለልተኛ የዲፕሎማሲ መርህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነትና አመኔታን አትርፎላታል ብለዋል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ከፍተኛ አማካሪ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ፤ ኢትዮጵያ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በአሜሪካ፤ በደርግ ዘመን ደግሞ በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረትና ቻይና ምህዋር ውስጥ ገብታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በሁለቱም ዘመናት የነበረው የመንግስታት የውጭ ግንኙነት ኢትዮጵያ ጎራ ለይታ ተሰልፋለች የሚል ፍረጃ ውስጥ አስገብቷት እንደነበር ያስታወሱት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ ይህ አካሄዷ አልጠቀማትም ብለዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው የገንቢ ገለልተኛ የዲፕሎማሲ መርህ ከሁሉም የዓለም ሀገራት ጋር መተባበርን መሰረት ያደረገ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መፍጠር አስችሏታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዓመታትን ያስቆጠረው የገንቢ ገለልተኛ የዲፕሎማሲ አቋሟ በዓለም ኃያላን አገራት ዘንድ መልካም ሥምና ተቀባይነት እያስገኘላት መሆኑን አምባሳደር ጥሩነህ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው የዲፕሎማሲ መስክ የመሪነት ሚናዋን ይዛ ለመቀጠል የገለልተኛ አቋም ዲፕሎማሲ አቋሟ ወሳኝ መሆኑን የሚገልጹት ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ፤ አቋሟ ከሁሉም ወገን ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት ለመፍጠር አስችሏታል ብለዋል፡፡
ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ካቀረቡት 40 ሀገራት መካከል ስድስቱ ሲመረጡ ኢትዮጵያ አንዷ መሆን የቻለችው በምትከተለው የገለልተኛ ዲፕሎማሲ አቋሟ የተነሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የልማት ፕሮጀክቶች በመገንባት ሀገራዊ እድገት ለማስመዝገብ ከዓለም ባንክም ሆነ ከብሪክስ 'ዘ ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ' የምታገኘውን ድጋፍ በአግባቡ መጠቀም ይኖርባታል ብለዋል፡፡