ቀጥታ፡

 የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና መረጃዎችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22/2015 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከግሪን አግሮ ሶሎሽንስ ሀላፊነቱ ከተወሰነ የግል ማህበር ጋር የግብርና መረጃዎችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ እና የግሪን አግሮ ሶሎሽንስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አብረሃም እንድሪያስ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን በዘመናዊ መንገድ የግብርና መረጃዎችን መሰነድ፣ ማስተላለፍ እንዲሁም ለአርሶ አደሩ የገበያ መረጃዎች በቀላሉ   እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

በተጨማሪም ስምምነቱ  አነስተኛ የእርሻ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል ሲሆን፤ ለሶስት ዓመታት የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል።

በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ትግራይ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 150 ወረዳዎች  በተለይ  በኩታ ገጠም በሚያመርቱ አካባቢዎች ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ፤ እንዳሉት በመንግስትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ግብርናን ትራንስፎርም ለማድረግ ተቋሙ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው።

በስምምነቱ መሰረት  የዋና ዋና ሰብሎችና የአትክልትና ፍራፍሬ መረጃዎችን ፣የተለያዩ ስነ-ምህዳር እና የአፈር ማዳበሪያ መረጃዎችን ዲጂታላይዝ ይደረጋሉ ብለዋል።

የማህበሩ  ስራ አስኪያጅ አብረሃም እንድሪያስ በኩላቸው የግብርና መረጃዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ 1 ሚሊየን 50 ሺህ አርሶደሮችን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የግብርና መረጃዎችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በሚሰራው ስራ ተጠቃሚ ለሚሆኑ 82 ሺህ ወጣቶች ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የነጻ ስልክ መስር 8028 ፣ በ''ለእርሻ ዲጂታል መተግበሪያ" የአንድ ማዕከል አገልግሎትና በሌሎችም  መረጃዎቹ ተደራሽ ይሆናሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም