የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው - ሙፈሪያት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው - ሙፈሪያት ካሚል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21/2015 (ኢዜአ)፦የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት በተለያዩ የትምህርት መስኮች በሁለተኛና በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከ3 ሺህ 650 በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል 73 የሱማሌላንድና የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች መሆናቸውም ተገልጿል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ወሳኝ ነው።
በመሆኑም ዘርፉ ለአገሪቱ ልማትና ብልጽግና የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ ከፍ ለማድረግና አገራዊ ለውጡን የበለጠ ለማፋጠን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናና ሌሎች ዘርፎችን አሰናስሎ ለማስቀጠል የሚያስችል የተለያዩ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን አገሪቱ ያላትን ጸጋ በአግባቡ መጠቀምና የዜጎችን ሕይወት ማሻሻል የሚችል የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት መደረጉን ነው ያስረዱት።
ከዚህ አንጻር ዛሬ የተመረቁት ተማሪዎች የዚህ ጥረት ፍሬ መሆናቸውን ገልጸው ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት ለአገሪቱ ዕድገትና ብልጽግና እንዲያውሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ከድር በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ዘርፎች ሙያተኞችን ለማብቃት ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በዛሬው ዕለትም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከ3 ሺህ 650 በላይ ተማሪዎችን ማስመረቅ መቻሉን ጠቁመዋል።
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ለረጅም ዓመታት በቴክኒክ ሙያ ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለአቶ ማሩ ተፈራ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል።