የአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ጠቅላይ መምሪያ ክልሉን ወደ ሰላም ለመመለስ እየተሠራ ያለውን የህግ ማስከበር ሥራ ገመገመ

ባሕር ዳር ፤ነሐሴ 21/2015(ኢዜአ)፦የአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ጠቅላይ መምሪያ የጎርጎራ ፕሮጀክት ጉብኝት ካደረገ በኋላ ክልሉን ወደ ሰላም ለመመለስ እየተሠራ ያለውን የህግ ማስከበር ሥራ ገምግሟል።

የኮማንድ ፖስቱ ከፍተኛ አመራሮች አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ ጀነራል አበባው ታደሰ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ ፣ የመከላከያ ከፍተኛ ጀኔራል መኮነኖችና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በተደረገው ግምገማ ክልሉ ከነበረበት የጸጥታ ችግር እየተላቀቀ ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ እየተከናወነ ያለው ህግ የማስከበር ሥራ ውጤታማ መሆኑን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴው መሻሻል ማሳየቱን አረጋግጧል።

በቀጣይ የተጀመረውን ህግ ማስከበር ሥራ በውጤታማነት በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ተሟላ ልማት እንዲገባ እየተሠራ መሆኑን ጠቅላይ መምሪያው አስታውቋል።

ኅብረተሰቡ የህግ ማስከበር ሥራው እንዲሳካ ላሳየው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያመሰገነ በቀጣይም በየደረጃው ካለው የህግ አስከባሪ እና የኮማንድ ፖስት አመራር ጋር በመሥራት የተለመደ አስተዋጽኦውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠቅላይ መምሪያው መልእክት ማስተላለፉን አሚኮ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም