በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለመጪው የትምህርት አመት ዝግጁ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለመጪው የትምህርት አመት ዝግጁ ሆነዋል
ጭሮ፤ ነሐሴ 21/2015 (ኢዜአ)-በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለመጪው የትምህርት ዓመት ዝግጁ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አወል አብደላ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ የትምህርት ተደራሽነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የሚረዱ ከ580 በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ብሎኮች ለመጪው የትምህርት ዘመን ተዘጋጅተዋል፡፡
ትምህርት ቤቶቹ በመጪው የትምህርት ዘመን በዞኑ ለሚገኙ ህፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ስርዓት መስፈርት ያሟላ ትምህርት መስጠት በሚችሉበት አግባብ መደራጀታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትውልዱ ከቅድመ መደበኛው እርከን አንስቶ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያስችል አክለዋል፡፡
ኃላፊው እንደሚሉት በዞኑ እነዚሁ የቅድመ መደበኛ ትምህርት መማሪያ ብሎኮች በታቀደላቸው ጊዜና ጥራት ተገንብተው መጠናቀቃቸው ህብረተሰቡ የልማት ተሳትፎውን በየእኔነት መንፈስ እንደተቀበለው አመላካች ነው ብለዋል፡፡
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶቹ በግል ከፍለው ማስተማር የማይችሉ ወላጆችን ችግር እየፈታ ያለ ትልቅ የህብረተሰብ ፕሮጀክት ሆኖ በየአመቱ እየቀጠለ መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡
አቶ አብደላ መሀመድ የተባሉ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ አነኖ ቀበሌ ነዋሪ በበኩላቸው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በህዝብ አቅም መከናወኑ ቀጣዩ ትውልድ ብሩህ ተስፋ እንዳለው የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡
"አካባቢያችን የአርብቶ አደር ወረዳ በመሆኑ ከአሁን ቀደም ህፃናት ለከብት እረኝነት እንጂ ትምህርት ቤት ብዙም ስለማይላኩ ከትምህርት የራቁ ናቸው" ይላሉ አቶ አብደላ፡፡
በቀጣይ ባለን አቅም ሁሉ በገንዘብም ሆነ በጉልበት በመሳተፍ የልጆቻችንን መማሪያ በመገንባት የመንግስት አጋርነታችንን እናሳያለን ብለዋል፡፡
የጭሮ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሒንዲሳር እስማኤል በበኩላቸው የቅድመ መደበኛ ትምህርት በህብረተሰብ ተሳትፎ መገንባቱ አቅም የሌላቸው ህፃናት ከትምህርት እንዳይስተጓጎሉ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ከመንግስት የሚወርዱ የልማት ጥያቄዎችን በጋራ እየመለሰ መሆኑ ለበርካታ ችግሮቻቸውም መፍትሄው መተባበር መሆኑንም መገንዘባቸውን ወይዘሮ ሒንዲሳር ጠቁመዋል፡፡