የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ወደ 50/50 እንዲሻሻል መደረጉ ላኪዎችን በማበረታታት የወጪ ንግዱንያጠናክራል - የላኪዎች ማህበራት - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ወደ 50/50 እንዲሻሻል መደረጉ ላኪዎችን በማበረታታት የወጪ ንግዱንያጠናክራል - የላኪዎች ማህበራት
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 21/2015(ኢዜአ):-ቁልፍ በሆኑ ወጪ ንግዶች ለተሰማሩ ላኪዎች የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ከ70/30 ወደ 50/50 እንዲሻሻል መደረጉ ላኪዎችን በማበረታታት የወጪ ንግዱን እንደሚጠናክር የላኪዎች ማህበራት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ነሐሴ 05/2015 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ባንኩ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ውሳኔዎችን ማሳለፉን መግለጻቸው ይታወቃል።
ከእነዚህ ውሳኔዎች መካከልም ቁልፍ በሆኑ የውጭ ንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ላኪዎችን ለማበረታታት የውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታ (forex surrender requirement) ከ70/30 ወደ 50/50 ቀመር እንዲሻሻል የተደረገበት አንዱ ነው ብለዋል።
በማሻሻያው መሰረት ላኪዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሬ ገቢ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ፣ 10 በመቶውን ለሚሰሩበት ባንክ እና ቀሪውን በራሳቸው የባንክ ሂሳብ እንዲያስገቡ ተወስኗል።
የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ላኪዎች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ክብረት ሙላት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታን ማሻሻሉ የወጪ ንግድ የግብይት ሥርዓትን ለመደገፍ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
በቁም እንስሳት ወጪ ንግድ ላይ እየተበራከተ በሚገኘው የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ የሚደርስባቸውን ኪሳራ በማካካስ የንግድ ስራቸውን እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት።
በመሆኑም የማሻሻያ ውሳኔው ግቡን እንዲመታና የወጪ ንግዱን እንዲያበረታታ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለወጪ ንግድ የህግ ተገዥነት በትኩረት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በህገ-ወጥ የቁም እንስሳት ወጪ ንግድ የተሰማሩ አካላት በአገሪቱ የተለያየ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የሰላምና ደህንነት ችግሮችን እንደመልካም አጋጣሚ እንደሚጠቀሙበት ጠቁመዋል።
ስለሆነም የአገር ሰላምና ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትብብር በመስራት የህገወጥ አካላትን ዓላማ ማክሸፍ ከኢትዮጵያውያን ላኪዎች ይጠበቃል ነው ያሉት።
የንግድና የግብር አገልግሎቱ በዲጂታል የቴክኖሎጂ ስርዓት እንዲሆን እየተደረገ ያለው ጥረት ጊዜ እና ወጪን በመቆጠብ ለስራቸው ቀልጣፋነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኘላቸው መሆኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ምርቶች መዳረሻ በሆኑ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎች ለወጪ ንግድ እድገት ከየአገራቱ ተቋማትና የንግዱ ማህበረሰብ ጋር በቅርበት መስራት እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ እና ቅባት እህል ላኪዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ኢዶ አብዲ፤ አብዛኛዎቹ የወጪ ምርት ላኪዎች በኢንዳስትሪ የተሰማሩና ግብዓት የሚያስፈልጋቸው ናቸው ብለዋል።
የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ከ70/30 ወደ 50/50 መሻሻሉ የኢንዱስትሪ ግብዓትና ጥሬ-እቃ ለማስገባት ሲያጋጥማቸው የነበረውን ችግር በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ማሻሻያው የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ ለመላክ አቅም እንደሚፈጥርና ላኪዎች ሊያጋጥማቸው የሚችልን ኪሳራ እንዲቋቋሙ የሚያደርግ ማበረታቻ በመሆኑም የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በቀጣይነትም የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ተወዳዳሪና ጥራት ያለው ምርት በመላክ ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ በትኩረት እንሰራለን ነው ያሉት።
ለዚህ ስኬትም በቂ ምርት እንዲኖር በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የንግዱ ማህበረሰብም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የተጀመረው የዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓት ላኪዎች ለሚያከናውኑት ዓለም አቀፍ ግብይት ፋይዳው የላቀ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
የወጪ ንግድ የዲፕሎማሲ ስራ የሚጠይቅ ዘርፍ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና አታሼዎች ለገበያ ትስስር መሳለጥና ለተሻለ የውጭ ምንዛሬ ግኝት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።