ቀጥታ፡

ተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ የህዳሴ ግድብ ድርድር በዛሬው እለት በግብፅ ካይሮ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2015(ኢዜአ):-ተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ የህዳሴ ግድብ ድርድር በዛሬው እለት በግብፅ ካይሮ ተጀምሯል።

የሶስትዮሽ ድርድሩ ከዚህ በፊት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አቡዳቢ ሲደረግ ቆይቶ ረቂቅ ስምምነት ማዘጋጀት ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ከዛ ወዲህ ድርድሩ ሳይካሄድ ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብድል ፋታህ አል ሲሲ ጋር ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረጉት ምክክር የግድቡን የውሃ ሙሌትና የውሃ አለቃቀቅ ደንቦችና መመሪያዎች በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል የደረሱትን መግባባት ተከትሎ ነው ውይይቱ የተጀመረው።


 

አምባሳደር ዶክተር ስለሺ በቀለ በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪ በመክፈቻ ንግግራቸው ይህ የሶስትዮሽ ድርድር በሶስቱ አገራት መካከል ትብብርን ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያ የአሁን እና የወደፊት ትውልድን ጥቅም ለማስጠበቅ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብት መሠረታዊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ግድቡ ለሶስቱ አገራት የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አምሳደር ዶክተር ስለሺ ኢትዮጵያ በፍትሀዊ እና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ አቋሟን አጠናክራና ድርድሩ በመግባባት እዲጠናቀቅ እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም