ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የአካባቢ ስርዓተ ምህዳርን በመጠበቅና ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ በምሳሌነት የሚጠቀስ የልማት ፕሮጀክት ነው - የመንግስታቱ ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የአካባቢ ስርዓተ ምህዳርን በመጠበቅና ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ በምሳሌነት የሚጠቀስ አስደናቂ የልማት ፕሮጀክት መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ኢ.ፒ.) ገለጸ።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስቀመጣቸውን የዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካትና ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በየማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች ነው።

ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በመተግበር በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

ዘንድሮ በተጀመረውና ለአራት ዓመታት በሚተገበረው ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በተመሳሳይ 25 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።


 

በመንግስታቱ ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ኢ.ፒ) የስርዓተ-ምህዳር ዘርፍ ዳይሬክተር ሱዛን ጋርድነር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ ለመስጠት አፋጣኝ ርብርብ ያስፈልጋል።

የመንግስትና የግሉን ዘርፍ የፋይናንስ ድጋፍ ተሳትፎ በማሳደግ የበካይ ጋዝ ልቀትን በሚፈለገው ደረጃ መቀነስ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትም የስርዓተ ምህዳር ጤናማነትን በማስጠበቅ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዜጎቿን ተጠቃሚ በማድረግ የአካባቢ ስርዓተ ምህዳርን ጤንነት ለማስጠበቅ በምሳሌነት የሚጠቀስ አስደናቂ የልማት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

በተለይም ዜጎች አስተባብሮ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ መርሐ ግብር መሆኑን ጠቁመው፤ የተባበሩት መግስታቱ ድርጅትም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።


 

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እስካሁን ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በብሪክስ 15ኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ህዝብን በማስተባበር እስካሁን ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን መናገራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም