ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ለባለብዙ ወገንና ለሁለትዮሽ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ጥረቷ እውቅና የሰጠ ነው-አምባሳደር ጀማል በከር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ለባለብዙ ወገንና ለሁለትዮሽ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ጥረቷ እውቅና የሰጠ ነው-አምባሳደር ጀማል በከር
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ለባለብዙ ወገንና ለሁለትዮሽ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ጥረቷ እውቅና የሰጠ ታሪካዊ ሁነት መሆኑን በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር ገለፁ።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አካታች፣ ፍትሐዊና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አዲስ የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር የበኩሏን ሚና አጠናክራ እንድትቀጥል የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት በሀገር ውስጥ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክ በተደረጉ ጥረቶች የተገኘና አፍሪካን የሚያኮራ ድል ነው ማለታቸው ይታወቃል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር፤ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት አገሪቱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ያስመዘገበችው ስኬት መገለጫ መሆኑን ገልፀዋል።
ከለውጡ ወዲህ የተከተለችው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መስኮች ስኬቶች እንዲመዘገቡ ማድረጉን ያሳየ ታሪካዊ ሁነት እንደሆነ በመጥቀስ።
ኢትዮጵያ ሁሉን አካታችና የበለፀገ የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር ያላት ቁርጠኝነት የብሪክስ ጥምረትን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ምስረታ ታሪካዊ ሚና ያላት መሆኗ፤ የብሪክስ አባል እንድትሆን አድርጓታል ያሉት አምባሳደሩ፤ ይህም ተደማጭነቷን ይበልጥ ከፍ እንደሚያደርገው ነው አንስተዋል።
አክለውም ለዓለም አየር ንብረት ተጽዕኖ ምላሽ ለመስጠት በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች ያለው እንቅስቃሴ እና የሰላም ማስከበር ተሳትፎዋም ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ እንደፀጥታው ምክር ቤት ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይበለጥ ወካይ፣ አሳታፊ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ከጥምረቱ አባላት ጋር በመተባበር ተፅዕኖ ለማሳረፍ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እምቅ የመልማት አቅምና ሰፊ አምራች የሰው ኃይል ያላት በመሆኗ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በኢኮኖሚ የትብብር መስኮች የላቀ ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን ያግዛል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የብሪክስ አባል ሀገራት ካላቸው ፈጣን የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ እድገት አንጻር ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ሽግግር እንድትፈጥርና አማራጭ የፋይናንስ ድጋፍ እንድታገኝ ሰፊ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
የወጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እና ለወጪ ንግዷ የገበያ እድል እንድታገኝ የሚያስችል በመሆኑ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም አለው ብለዋል።
አምባሳደር ጀማል የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት በባለብዙ ወገንና በሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ መድረኮች የሚደረጉ ጥረቶች ስኬታማ መሆናቸውን ያሳየ መሆኑን ገልዋል።
በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል አገራት ጉባኤ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ አርጀንቲና፣ ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ አዲስ የብሪክስ አባል ሀገራት እንዲሆኑ መወሰኑ ይታወቃል።