የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 21/2015 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ከኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ ጋር ያከናውናል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በዩጋንዳ ንጄሩ ከተማ በሚገኘው ‘FUFA Technical Center Stadium’ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ንግድ ባንክ በምድብ አንድ በ10 ነጥብና በ13 የግብ ክፍያ አንደኛ በመሆን ምድቡን በመሪነት አጠናቋል።
ተጋጣሚው ቪሂጋ ኩዊንስ በበኩሉ በምድብ ሁለት ስድስት ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ መጨረሱ ይታወቃል።
ንግድ ባንክ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ነሐሴ 24/2015 በፍጻሜው ከብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ እና ከታንዛንያው ጄኪቴ ኩዊንስ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በጄኪቴ ኩዊንስና ቡጃ ኩዊንስ መካከል ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
የውድድሩ አሸናፊ ክለብ የሴካፋ ዞንን ወክሎ በኮትዲቭዋር አቢጃን በሕዳር ወር 2016 በሚካሄደው ሶስተኛው የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል።