ቀጥታ፡

የቅድመ መደበኛ ትምህርት መስፋፋት ለትምህርት ጥራት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው - ወላጆች

መቱ ፤ነሐሴ 21/2015 (ኢዜአ)፡- የቅድመ መደበኛ ትምህርት መስፋፋት በትምህርት ጥራትና ተማሪዎች ብቃት ላይ ይስተዋል የነበረውን ችግር የሚቀርፍ በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባው ወላጆች ገለፁ።

በኢሉ ባቦር ዞንም ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ትኩረት በመስጠት የቡኡረ ቦሩ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በኅብረተሰቡ ተሳትፎና በበጎ ፈቃደኞች የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የዞኑ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ነው።

የቅድመ መደበኛ ትምህርት ከዚህ ቀደም በከተሞች አካባቢ በተለይም በግል ትምህርት ቤቶች ብቻ ተወስኖ እንደቆየ ይታወቃል።

በመሆኑም ዕድሜያቸው ለመደበኛ ትምህርት ያልደረሱ ሕፃናት የዕድሉ ተጠቃሚ ያልነበሩ በመሆናቸው በትምህርት ብቃታቸው ላይ ተፅዕኖ እንደነበረው ይነሳል።

በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት "ቡኡረ ቦሩ" በሚል ንቅናቄ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከፈቱ በሚገኙ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መሰጠት የጀመረው ትምህርት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል ነዋሪዎቹ።

በዞኑ የሁሩሙ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሚሊዮን ነጋሽ እንዳሉት ዕድሜያቸው ለመደበኛ ትምህርት ያልደረሱ ሕፃናት የትምህርት ቤት አከባቢን እንዲላመዱ ማድረግ ለዋናው ትምህርት ዝግጁ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

በዚህ ደረጃ መቅሰም ያለባቸውን መሰረታዊ ነገሮች ስለሚያገኙ ለመደበኛ ትምህርት ብቁ የሚሆኑበት ሁኔታን የሚፈጥርላቸው በመሆኑ ትልቅ እገዛ ያደርግላቸዋል ።

ሌላው ነዋሪ አቶ ገዛኸኝ ጊጆ  የቅድመ መደበኛ ትምህርት ከዚህ ቀደም በመደበኛነት የሚታወቀው ከተሞች አካባቢ በግል ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆኑን አንስተው፤ አሁን በመንግስት ትምህርት ቤቶች መሰጠት መጀመሩ ሁሉንም ሕፃናት ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።


 

ከዚህ ቀደም ዕድሉን ሲያገኙ ያልነበሩት ቀጥታ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት የሚገቡ በመሆኑ ብዙ ፈተና ያጋጥማቸው ነበር ያሉት አቶ ገዘኻኝ፤ አሁን ላይ በተሰጠው ትኩረት  ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር ተስፋ ሰጪ  ነው ብለዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ እንዳለ በዳዳ በአከባቢው የሚታወቀው ቅድመ መደበኛ ትምህርት አቅሙ ያላቸውን የተወሰኑ ሕፃናትን ብቻ የሚያሳትፍ የግል ትምህርት ቤት ብቻ ነበር ይላሉ።

ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በተለይም በክልሉ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ ትምህርቱ መሰጠት መጀመሩ ለትውልዱ ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ መደበኛ ትምህርትን የሚቀላቀሉ ሁሉም ሕፃናት እኩል ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉበትን እድል ማግኘታቸው ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ፣ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥም ወሳኝ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በነባር ትምህርት ቤቶች ውስጥ በተለዩ ክፍሎች እንዲሁም በየወረዳዎች እየተገነቡ በሚገኙ የቡኡረ ቦሩ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መጠናከር ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው በማከል። 

በኢሉ ባቦር ዞንም ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ትኩረት በመስጠት የቡኡረ ቦሩ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በኅብረተሰቡ ተሳትፎና በበጎ ፈቃደኞች የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የዞኑ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አብዲሳ ናቸው።

በዚህም አስካሁን ከ42 በላይ የቡኡረ ቦሩ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በዞኑ ተገንብተው ስራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በነባር የመደበኛ ትምህርት ቤቶች ክፍሎች ተለይተው ዕድሜያቸው ለመደበኛ ትምህርት ያልደረሱ ሕፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በ2016 የትምህርት ዘመንም ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዕድሜያቸው አ4 እስከ 6 ዓመት የሆናቸውን ሕፃናት ለቅድመ መደበኛ ትምህርት የመቀበል ዕቅድ ተይዞ ምዝገባ የተጀመረ መሆኑንም ነው የተናገሩት።


 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2016 ዓ.ም በዞኑ በአጠቃላይ ከ200 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመደበኛ ትምህርት ለመቀበል ዕቅድ መያዙንና በሁሉም ወረዳዎች ከነሐሴ 15 ቀን 2015ዓ.ም ጀምሮ ምዝገባ መካሄድ መጀመሩን ገልፀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም