ቀጥታ፡

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ማብቂያ ቀን ኢትዮጵያ የምትወዳደርባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 21/2015 (ኢዜአ) ፦ ዛሬ ፍጻሜውን በሚያገኘው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ይደረጋሉ።

ከማለዳው 2 ሰዓት የወንዶች ማራቶን የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ አትሌት ታምራት ቶላ፣አትሌት ፀጋዬ ጌታቸው፣አትሌት ልዑል ገብረስላሴ እና አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ ይሳተፋሉ።

አትሌት ታምራት በአሜሪካ ኦሬጎን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ ይታወሳል።

ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ በሚካሄደው የ5 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ፣አትሌት በሪሁ አረጋዊና አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት ይሳተፋሉ።

ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ10 ደቂቃ የ3 ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ አትሌት ሲምቦ አለማየሁ፣ አትሌት ሎሚ ሙለታና አትሌት ዘርፌ ወንድምአገኝ የሚወዳደሩ ይሆናል።

በተያያዘም ትናንት በተካሄደው የ5 ሺህ ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል አልቀናቸውም።

አትሌት እጅጋየሁ ታዬ፣አትሌት መዲና ኢሳና አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ከአምስተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ 13ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቃለች።

የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት አትሌት ፌዝ ኪፕዬጎን አንደኛ በመውጣት አሸንፋለች።

ኢትዮጵያ እስከ አሁን በሻምፒዮናው 2 የወርቅ፣ 4 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም