የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት የአፍሪካን አጀንዳና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የሚረዳ ነው- በአልጀዚራ የጥናት ማዕከል የምርምር ግንኙነት ኃላፊ ቴምቢሳ ፋኩዴ

878

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የብሪክስ ቡድን አባል አገር መሆኗ የአፍሪካን ድምጽ ከማሰማት አልፋ አሕጉራዊ ጥቅሞችን ታስጠብቃለች የሚል እምነት እንዳላቸው በአልጀዚራ የጥናት ማዕከል የምርምር ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ቴምቢሳ ፋኩዴ ገለፁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በብዙ ዓለም አቀፍ መድረኮች ያላቸው ላቅ ያለ ተቀባይነት የአፍሪካን አጀንዳ ያሳከሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። 

በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ከሚዘግበው ኢ-ኒውስ ቻናል አፍሪካ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት የአፍሪካን ጥቅሞች ለማስጠበቅ የሚረዳ ነው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን በብሪክስ አባል አገራት በሚነሱ ጉዳዮች ላይ የአፍሪካ አጀንዳን በማንሳት አሕጉራዊ ጥቅሞች እንዲጠበቁ የማድረግ ብቃት እንዳላት ተናግረዋል።

ቴምቤሳ ፋኩዴ አክለውም ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤዎችን በማቀንቀን አፍሪካዊ አንድነት እንዲጠናከር የምትሰራ አገር መሆኗ ለአባልነት ይበልጥ ተመራጭ አድርጓታል ብለዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል የገነባች አገር መሆኗ ደግሞ በብሪክስ አባል አገራት ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ካለፉት ሃያ ዓመታት ወዲህ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለች ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ይህን ዕድገት ማስቀጠል የምትችል አገር መሆኗ ለመመረጧ በዋቢነት አንስተዋል። 

በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል አገራት የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ 6 አገራት በአባልነት መቀበሉ የሚታወቅ ነው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም