የፌዴራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የሙስና እና ብልሹ አሠራር ተጋላጭነትን ለመከላከል ለትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታ ትኩረት መስጠቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የሙስና እና ብልሹ አሠራር ተጋላጭነትን ለመከላከል ለትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታ ትኩረት መስጠቱን ገለጸ

ሀዋሳ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) --በሀገሪቱ የሙስና እና ብልሹ አሠራር ተጋላጭነትን ለመከላከል እንዲቻል ለትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን የፌዴራል የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
ሀገር አቀፍ የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ትስስር ጉባኤ ዛሬ በሀዋሳ ተካሂዷል።
የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በሀገሪቱ ለሙስና መስፋፋት አንዱና መሰረታዊ ምክንያት የዜጎች የሥነ ምግባር ግድፈት ነው።
ዜጎች በትክክለኛ ሥነ-ምግባር ለእውነት የሚሰሩና የሚኖሩ፣ የሀገራቸውንና የቤተሰባቸውን ሀብት የማይሰርቁ፣ በሰሩትና በለፉት ልክ ለመክበር የሚተጉ ሆነው እንዲወጡ በሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመሆኑም ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ተልእኮ መነሻነት ተቋም ተኮርና ችግር ፈቺ የሆነ የሥነ-ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ስልጠና በ2016 ዓ.ም ለመስጠት አቅጣጫ ማስቀመጡን አቶ ወዶ አስታውቀዋል።
''እዚህ ላይ ጤናማ ስራ ከተሰራ ማህበረሰቡን የምንለውጥበትን እድል እናሰፋለን'' ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ለዚህም በፌዴራልና በክልሎች ለሚገኙ አመራሮችና ለመንግስት ስራተኞች ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ በተቋማት ተግባራዊ እንዲደረግ ኮሚሽኑ በሀገር ደረጃ የስነ-ምግባር ግንባታ እና የፀረ-ሙስና ተግባራትን የመምራትና የማስተባበር ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አቶ ወዶ አመልክተዋል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት የህዝብ ተመራጮችን፣ የመንግስት ተሿሚዎችንና የመንግስት ሰራተኞችን፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ኃላፊዎችና ሰራተኞች ሃብታቸውን እንዲያሳውቁ፣ እንዲያስመዘግቡ፣ ትክክለኛነቱ እንዲረጋገጥና መረጃው ተደራጅቶ ተደራሽ ይሆናል ብለዋል።
የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በተጀመረው የጸረ-ሙስና እንቅሰቃሴ ለውጥ መታየት መጀመሩን ገልጸዋል።
''በዚህ ሂደት ከዜጎች ሙስናና ሙስናን የሚያመላክቱ በርካታ ጥቆማዎችን ተቀብለናል'' ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ይህንን መነሻ በማድረግ የተወሰኑ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውቀዋል።
በእንቅስቃሴው በሙስና የባከነ ሀብት እየተመለሰና ወንጀለኞች እየተቀጡ መሆኑን ጠቁመው፣ ''በቀጣዮቹ ዓመታት በልዩ ሁኔታ ሙስና መከላከል ስራ ይሰራል'' ብለዋል።
በመሆኑም በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ዘመቻ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላትና የትውልድ ስነ-ምግባር ግንባታ ስራውን በማጠናከር ስራውን ወደ ፊት ለማሻገር በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላትር ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጀማል ረዲ በሰጡት አስተያየት የህብረተሰቡ ነባር እሴቶች እየተሸረሸሩ በመምጣታቸው ሙስና እየተስፋፋ መምጣቱን ገልጸዋል።
በተለይ ሙስና ለግጭቶችና ለቀውስ ዋነኛ መንስኤና መገለጫ እየሆነ በመምጣቱ ወጣቱን ትውልድ ስነ-ምግባር በተላበሰ መንገድ ለመቅረጽ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ይሰራል ብለዋል።
በዚህ ረገድ በመዲናዋ ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተግባር ተኮር ስልጠና በየደረጃው ለመስጠት ግብ መያዙን አቶ ጀማል አስታውቀዋል።
የኦሮሚያ ክልል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብደላ ኦገቴ ውይይቱ በአዲሱ በጀት ዓመት ሙስናን በጋራ ለመከላከልና ለቀጣይ ስራ አቅም እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
በቀጣይም ኮሚሽኑ የሙስና አደገኝነትና ልማት አደናቃፊ መሆኑን የሚያመላክት አስተሳስብ ለማስረጽ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር በመስራት ለውጥ ለማምጣት ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ የሃብት ምዝገባና ትክክለኛነትን የማረጋገጡን ስራ ከማኑዋል ወደ ዲጂታል በመቀየር ጠንካራ የሙስና የመከላከል ተግበራት ለማከናወን መታቀዱንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
''እውቀት መር አመራርነት ለላቀ የፀረ ሙስና ትግል" በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀናት በተሰናዳው በዚሁ ጉባዔ ላይ የዘርፉ ሀገር አቀፍ የ2016 ዓመታዊ መሪ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በፀረ-ሙስና ትግል እንቅስቃሴ ላይ የህዝብ አስተያየት ለማወቅ የተከናወነ የዳሰሳ ጥናት እና የተቋማዊ አደረጃጀት ገለልተኝነትና ብቃትን ለማሻሻል የተከናወነ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።