ቀጥታ፡

የአማራ ክልል ፈተናዎች ሲገጥሙት በጽናት አልፏል፤ አሁንም የገጠመውን ችግር የመወጣት አቅም አለው- ምክትል ርዕስ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ.ር / ኢንጂነር)

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 ( ኢዜአ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በዓለ ሲመት በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል። በበዓለ ሲመቱ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ.ር /ኢንጂነር) በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ሁኔታ ስጋት ውስጥ ከቷቸው እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ በጋራ በተሠራው ሥራ ሰላማዊ አየር መተንፈስ ተጀምሯል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ፈተናዎች ሲገጥሙት በጽናት አልፏል፤ አሁንም የገጠመውን ችግር የመወጣት አቅም አለው፤ የአመራር ጥበብ ያለበት ሕዝብ በመሆኑ ችግሩን ያልፈዋል ብለዋል። ክልሉ ችግሮችን የመፍታት አቅም እና ጥበብ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል። ባለፉት ዘመናት የመጣበትን ጥበብና አቅም ከተጠቀምን አሁንም ችግሩን ይፈታል ብለዋል። 

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ እንዲፈቱ እንሠራለን ነው ያሉት። አሁን ላይ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የተሻለ አውድ መኖሩንም አንስተዋል።

አሁን ወደ መሪነት ለመጡ መሪዎች ጊዜው ከባድ ቢመስልም በቁርጠኝነት ከሠሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን መፍታት ይቻላል ብለዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሮችን ፈትተው ለሌሎች ምሳሌ እንደሚኾኑ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

ብዙዎች መሥዋእትነት በመክፈል ለክልሉ ሕዝብ መሥራታቸውንም ተናግረዋል።

በማኀበራዊ ሚዲያ ችግርን የሚያባብሱና ቁርሾን የሚፈጥሩ አካላት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው  መናገራቸውነ የአሚኮ ዘገባ ያሳያል። 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የሚቻለውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም