ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁማ እያስመዘገበች ያለው ስኬት በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተቀባይነት እንዲጨምር አድርጓል - የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁማ እያስመዘገበች ያለው ስኬት በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተቀባይነት እንዲጨምር ማድረጉን የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬት የብሪክስ አዲስ አባል አገራት መሆናቸው ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ፈተናዎችን ተቋቁማ በተለይ በኢኮኖሚውና ዲፕሎማሲ መስክ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቧን ተናግረዋል፡፡

ይህም የብሪክስ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት መስራች አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህም በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መስክ ያላትን የቆየ ታሪክ የሚያመላክት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም ለብሪክስ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗ የኢኮኖሚ ትብብሮችን ከማጠናከር ባሻገር በባለብዙ የትብበር መድረኮች ላይ ያላት ተሳትፎ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት፡፡

በተጨማሪም የተጀመሩ የልማትና የዲፕሎማሲ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደሚያግዝም እንዲሁ፡፡

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች የሚገባትን ቦታ እንድትይዝ ከፍተኛ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያ ተደማጭነት እየጨመረ መምጣቱ አገሪቱ በትክክለኛ ጎዳና ላይ መሆኗን እንደሚያመላክት ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር የተጀመሩ የልማትና የዲፕሎማሲ ድሎችን ማስቀጠል ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ከዚህ በተሻለ መልኩ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያላት ድርሻ እንዲጎለብት መስራት እንደሚገባ በመግለጽ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም