አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ በውሃ እና ኢነርጂ ዘርፍ የዲጅታል ኢኮኖሚን እውን ማድረግ የሚያስችል አቅም እንዳላት ያሳያል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ በውሃ እና ኢነርጂ ዘርፍ የዲጅታል ኢኮኖሚን እውን ማድረግ የሚያስችል አቅም እንዳላት ያሳያል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የውሃ እና ኢነርጂ አውደ ርዕይ ኢትዮጵያ የዲጅታል ኢኮኖሚን እውን ማድረግ የሚያስችል እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እንዳላት ያሳየ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር "የውሃ ሀብታችን ለብልፅግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀውን አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል፡፡
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የዲጅታል ኢኮኖሚን መገንባት፣ የሥራ ዕድል መፍጠር እና ተኪ ምርቶችን ማምረት የሚያስችሉ ጸጋዎች ባለቤት ነች፡፡
በሳይንስ ሙዚዬም የተዘጋጀው የዲጅታል ኢኮኖሚ አውደ -ርዕይም ኢትዮጵያ የዲጅታል ኢኮኖሚን እውን ማድረግ የሚያስችል እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እንዳላት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር የቴክኖሎጂ መዋቅራዊ ዝግጅት በማድረግ ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሀገርን ማሳድግ የሚችሉ መሆናቸውን አይተናል ብለዋል፡፡
የዲጅታል ኢኮኖሚን ለመገንባት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ምርቶችን የሚያስቀሩ ትላልቅ ፕሮጀክት እየተሰሩ መሆኑን አይተናል ብለዋል፡፡
የኃይል አቅርቦትና ሥርጭቱን ለማሻሻል የነፋስ፣ ጸሀይ እና የሌሎች ታዳሽ ኃይል አማራጮችን መጠቀም እንደሚቻል ያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የውሃ እና ኢነርጂ አውደ ርዕዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ መክፈታቸው ይታወሳል፡፡