የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚን በአፍሪካ እሴቶች የተቃኘ አህጉራዊ ተቋም ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚን በአፍሪካ እሴቶች የተቃኘ አህጉራዊ ተቋም ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እያከናወነ ነው
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ በአፍሪካ እሴቶች የተቃኘ አህጉራዊ ተቋም ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ አስታወቀ።
አካዳሚው ስሙን የሚመጥን በፓን-አፍሪካኒዝም የተቃኘ አህጉራዊ ተቋም ለመሆን የሚያስችል አዲስ ተቋማዊ የማስተር ፕላን ንድፈ ሃሳብ ይፋ አድርጓል።
በአካዳሚው ማስተር ፕላን ንድፈ ሃሳብን ለማቅረብ ከተወዳደሩ 14 የኪነ-ሕንፃ ባለሙያዎች መካከል ለአሸናፊው እና ለተሳታፊዎቹ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
የአካዳሚው ምክትል ርዕሰ አካዳሚ ዶክተር ወንድዬ ለገሰ፤ አካዳሚው በፓን አፍሪካኒዝም ይዘት ለትውልድ ተሻጋሪ ተቋም የመሆን ግብ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
አዲሱ መሪ ፕላን ተቋማዊ ገጽታውን ለመገንባት እንደሚያስችለው ነው የጠቆሙት።
አካዳሚው ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ለውጥ የሚበጁ አመራሮች የሚፈልቁበት የሀሳብ ልዕልና ማዕከል በመሆኑ፤ የአካዳሚው ገጽታ የአፍሪካን እሴቶች ያንፀበረቀ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ማስተር ፕላኑ አካባቢያዊ ሁኔታውን ታሳቢ ያደረገ፣ የመሬት ሀብቱን በቅጡ የተጠቀመ፣ አፍሪካዊ ገፅታ ያለው ዘመን ተሻጋሪ ሕንፃ ለመገንባት እንደታቀደም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ሀብታሙ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ማስተር ፕላኑ የአካዳሚውን አህጉራዊ የልህቀት ተቋም የመሆን እንቅስቃሴን ለማሳካት የራሱ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የማስተር ፕላን ሀሳቡ በውድድር መደረጉ በምህንድስና መስፈርቶችን ያሟሉ ግንባታዎችን ለማካሔድ ብሎም ተቋማዊ ገፅታ በመገንባት ሁነኛ ፋይዳ እንደሚኖረው እንዲሁ።