ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ያላት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ በጤናው ዘርፍ ጠንካራ የትብብር ማዕቀፍ እንዲኖር የሚያግዝ ነው- ዶክተር ሊያ ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ያላት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ በጤናው ዘርፍ ጠንካራ የትብብር ማዕቀፍ እንዲኖር የሚያግዝ ነው- ዶክተር ሊያ ታደሰ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ያላት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ በጤናው ዘርፍ ጠንካራ የትብብር ማዕቀፍ እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል አገራት ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬት የብሪክስ አዲስ አባል አገራት መሆናቸው ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ባለፉት ጊዜያት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ሲካሄድ መቆየቱን መጠቆማቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗ የኢኮኖሚ ትብብሮችን ከማስፋት ባለፈ በዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ያላት ተደማጭነት እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
ይህም በተለያዩ የትብብር ማዕቀፎች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያግዝ ነው የተነገረው፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወደ ዕድል በመለወጥ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ትልቅ እምርታን እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ብሪክስ ግዙፍ ኢኮኖሚ በመመስረት ላይ ያሉ አገራትን የሚወክል ትብብር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በተለይ ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ከአባል አገራቱ ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ትልቅ እድል ያለው መሆኑን ጠቁመው በዲፕሎማሲው ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላት ተሰሚነት ከፍ እንዲል የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአባል አገራቱ መካከል የሚፈጠረው ትብብር ለጤናው ዘርፍም እድል መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ በተለይ በመድሃኒትና ክትባት ምርት ላይ ያለው ትብብር እንዲጎለብት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ለሌሎች አገራት የምታበረክተው ትልቅ አቅም እንዳላት ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ የጤና ስርዓቷን ከመገንባት አንጻር ከበርካታ አገራት ጋር የደረሰችውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ስምምነቶችን የምታጠናክር መሆኗን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚኖረው ትብብርም የፋይናንስ አቅምን ከማሳደግ ባሻገር በጤናው ዘርፍ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እንደሚያግዝ አውስተዋል፡፡
ይህም በተለይ ታላላቅ ስፔሻሊቲ ሆስፒታሎች እንዲስፋፉ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡