ቀጥታ፡

ብሪክስ (BRICS)፣ የዓለም አቀፍ ስርዓትና መዋቅሮች ላይ ያስከተላቸው ለውጦች እና ለታዳጊ ሀገራት ያላቸው እንድምታ

ብሪክስ (BRICS)፣ የዓለም አቀፍ ስርዓትና መዋቅሮች ላይ ያስከተላቸው ለውጦች እና ለታዳጊ ሀገራት ያላቸው እንድምታ

  1. መግቢያ

እ.አ.አ 2001 ጂም ኦንየል የተባለ የአሜሪካው ጎልድማን ሳችስ ባንክ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ ብሪክስ የሚለውን ቃል ጥቅም ላይ ያዋለው ሲሆን፤ በወቅቱ ብራዚል፣ ራሺያ፣ ህንድ እና ቻይና የመሳሰሉ ሀገራት እያስመዘገቡት የነበረውን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመግለፅ ተጠቅሞበታል፡፡ ይህ ባንክ የእነዚህ ሀገራት የሕዝብ ብዛት፣ ዴሞግራፊያዊ ሁኔታዎች እና ግሎባላይዜሽን ላይ ያላቸው እንድምታ የመሳሰሉ መገለጫዎችን በመመልከት በቅርብ ዓመታት ውስጥ የአውሮፓ ሕብረት የገበያ መጠንን ሊበልጥ የሚችል እምቅ ኢኮኖሚያዊ ዐቅም አላቸው በማለት ተንብይዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ባንኩ ቻይና፣ ህንድ፣ ብራዚል እና ራሺያ እ.አ.አ 2050 ላይ በቅደም ተከተል አንደኛ፣ ሦሥተኛ፣ አምስተኛ እና ስድስተኛ የዓለማችን ኢኮኖሚ ባለቤት ይሆናሉ የሚል ትንበያን አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን የብሪክስ ሀገራት ጥምረት መደበኛ በሆነ መልኩ ዕውን የሆነው እ.አ.አ 2006 ላይ በኒውዮርክ ከተማ ሲሆን፤ በወቅቱ ሲካሄድ ከነበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ ጎን ለጎን የብራዚል፣ ራሺያ፣ ህንድ እና ቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ያካሄዱትን ስብሰባ ተከትሎ ነው፡፡ እ.አ.አ 2011 በተካሄደው የጥምረቱ ሦስተኛው ጉባኤ ላይ ደቡብ አፍሪካ አባል ሆና አምስት አባላት ወዳሉት ጥምረት የተሸጋገረ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎ የጥምረቱ ስያሜም BRIC ከሚለው ወደ BRICS ተለውጧል፡፡

የብሪክስ ጥምረት ዓላማ የሚመሠረተው የአባል ሀገራቱ የረዥም ጊዜ የጋራ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማረጋገጥ ሲሆን፤ ይህም የዓለማችንን ኢኮኖሚያዊ እና ፋይናንሳዊ አሠራሮችን እና ንድፎችን ሪፎርም ማድረግ፣ የዓለም አቀፍ ሕግ መርሖችንና ስታንዳርዶችን ማጠናከር እና የኢኮኖሚያቸው የተለያዩ ሴክተሮች አሟሟይነትን (complementarities) መደገፍ ያካትታል፡፡ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የጥምረቱ ዓላማዎች እየሰፉ የመጡ ሲሆን፤ በሂደትም ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ባሻገር እንደ የአካባቢ አየር ፀባይ ለውጥ፣ ዘላቂ ዕድገት፣ የምግብና ኢነርጂ ደኅንነት፣ ጤና፣ የዓለምአቀፍ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ተቋማት ሪፎርም እና ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ጥምረቱ በእነዚህ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ እያካሄዳቸው በሚገኙ የተባበሩ ሥራዎች አማካኝነት በዓለም አቀፍ ስርዓቱ እንደ አጠቃላይ እና በዓለማችን ደኅንነት በተለይ የራሱ የሆኑ ተፅዕኖዎችን እያስከተለ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በዚህ የንስር መፅሄት የመድረክ ዓምድ የብሪክስ ሀገራት ንቅናቄ በወቅታዊው የዓለም አቀፍ ስርዓት እና መዋቅሮች ሪፎርም ያለውን ሚና እና ለታዳጊ ሀገራት የሚያበረክተውን አንድምታ በደምሳሳው ይዳሰሳል፡፡

  1. ብሪክስ እና ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ስርዓት

የዚህ ዘመን ዓለም አቀፍ ስርዓት አንዱ መገለጫ ባሕሪ ብዛት ያላቸው ቁልፍ ተዋንያን በመሆን ብቅ እያሉ የሚገኙ ኢኮኖሚዎች (emerging economies) ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እያደገ መምጣት ነው፡፡ በመግቢያው ላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ብሪክስ (BRICS) የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው የብራዚል፣ ራሺያ፣ ህንድ እና ቻይና እያደገ በመሄድ ላይ የነበረውን የኢኮኖሚ እምቅ ዐቅም ለመግለፅ ጎልድማን ሳችስ በተባለ ተዋቂ ተቋም እ.አ.አ በ2001 ሲሆን፤ ከዚህ ጊዜ አንሥቶ ይህ ቃል የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ካደጉ ሀገራት በማደግ ላይ ወደሚገኙ ዋና ዋና ሀገራት እያደረገው የሚገኘውን ሽግግር ለማመላከት በስፋት እያገለገለ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት ይህ ተቋም እ.አ.አ 2032 ላይ የብሪክስ ሀገራት አጠቃላይ ኢኮኖሚ ከቡድን 7 ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ዐቅም ጋር እኩል ደረጃ ላይ ይደርሳል በማለት ትንበያውን አስቀምጧል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ እ.አ.አ 2011 ላይ ደቡብ አፍሪካ የብሪክስ አባል መሆኗን ተከትሎ የዚህ ስብስብ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ከታሰበው በላይ ሆኖ ይገኛል፡፡

የብሪክስ ሀገራት ጥምረት እየጠነከረ እንዲመጣ እያደረጉ ከሚገኙ ምክንያቶች መካከል እነዚህ በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኗቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋት አካባቢያዊ የሆኑ ጥምረቶች በቂ አለመሆናቸውን መገነዝባቸው አንዱ ነው፡፡ ሌላኛው ምክንያታቸው ደግሞ በአካባቢያቸው ያላቸው የተፅዕኖ አድማስ ዙሪያ በዓለም ሀያላን ሀገራት እና ሌሎች አካባቢያዊ ተዋንያን ለሚያጋጥመው እክል ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ እነዚህን ተግዳሮቶች በመቋቋም አካባቢያዊ ትብብርን ከማጠናከር ባሻገር ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኗቸውን ለማስፋት የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ አንድምታ ያለው ስትራቴጂ መከተል እንደሚገባቸው ተገንዝበዋል፡፡ ይህንን ዓለም አቀፍ ስትራቴጂን በመከተል የብሪክስ ሀገራት በተለይ የታዳጊው ዓለም ጠንካራ የንግድ አጋሮች ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ የልማት ወዳጆች ጭምር መሆናቸውን ለማሳየት በሚያስችላቸው መንገድ ዓለም አቀፍ ሚናቸውን ትራንስፎርም ለማድረግ እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡

ባለፉት ዓሥርት ዓመታት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የብሪክስ አባል ሀገራት በዓለማዊ ጉዳይ ዙሪያ ያላቸው ንቁ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ለመታዘብ ችሏል፡፡ በግል ደረጃ የብሪክስ አባል ሀገራት ቁልፍ አካባቢያዊ ተዋንያን እየሆኑ፣ በአካባቢያቸው ደኅንነት ዙሪያ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ እና ለዚህም አካባቢያዊ ተቋማት እና ከዋና ዋና የውጭ ተዋንያን ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ትብብር በመጠቀም ላይ መሆናቸው በግልፅ የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ብሪክስ እንደ ጥምረት የዓለም አቀፍ የአካባቢ አየር ፀባይ ለውጥ ድርድሮች ላይ በቅርበት በመሥራት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤትን ሪፎርም በማነቃነቅ፣ የአፍሪካ ሀገራት ልማትን በመደገፍ እና ታዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ ስርዓት ላይ ያላቸውን ሚና በማሳደግ ፍትሐዊ የሆነች ዓለም ለመፍጠር የሚደረገውን ዘመቻ በማስተባበር ላቅ ያለ ተፅዕኖ ለመፍጠር በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ተራማጅ የሆነ እንቅስቃሴ የሚያመላክተን በማደግ ላይ የሚገኙ ኃይሎች (emerging powers) በዓለም አቀፍ ስርዓቱ የሚኖራቸው የመጪው ዘመን እጣ ፈንታቸው እጅግ በተሳሰረ እና በተባበረ ሚናቸው ላይ የሚመሠረት መሆኑን በትክክል ማየት መቻላቸውን ነው፡፡ እነዚህ ሀገራት የራሳቸውን እና የሌሎች ታዳጊ ሀገራትን ውስጣዊ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሯቸው ጥቅሞች መረጋገጥ የሚችሉት ውጫዊውን አካባቢ በተመለከተ በሕብረት እንደ አንድ ተዋንያን ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸው አደረጃጀት መኖር አስፈላጊትን በጥልቀት መገንዘብ ችለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ይህ ጥምረት በዓለም አቀፍ ስርዓቱ ውስጥ በተለይ ለታዳጊ ሀገራት በሚያመች መልኩ ሪፎርም ለማካሄድ ትልቅ እንድምታ ያለው እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡

  1. ብሪክስ እና በዓለም አቀፍ ደኅንነት ያለው ሚና

ቅድመ ቀዝቃዛው ጦርነት እና ድኅረ ቀዝቃዛው ጦርነት ያለውን የዓለማችን ሁኔታ ካነፃፀርን ብዛት ያላቸው ለውጦችን የምናይበት ነው፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት እንደነበረው የአሜሪካና ሶቪየት ሕብረት ዓይነት በሁለት ጎራዎች የተከፈለ ፉክክር በዚህ ዓለማዊ ሁኔታ በስፋት አንመለከትም፡፡ የርዕዮተ ዓለም (አይዲዮሎጂ) ፉክክር ያለፈው ዘመን ታሪክ ሆኗል፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሶሻሊስት የነበሩ ሀገራት በገበያ መር ኢኮኖሚ ተተክተዋል፡፡ በምዕራቡም ሆነ በምሥራቁ የዓለማችን ክፍል ዴሞክራሲ የአብዛኛዎቹ ሀገራት መፈክርና መርሕ ሆኖ ይገኛል፡፡ ባለ ሁለት ዓለም ዋልታ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታሪክ ሊሆን ችሏል፡፡

የሶቪየት ሕብረት መፈረካከስን ተከትሎ አሜሪካ የሌሎች ሀገራትን እንቅስቃሴ እና እርምጃ ከራሷ ብሔራዊ ጥቅም አንፃር የምትቃኝበትና ተፅዕኖ የምታደርስበት ባለ አንድ ዋልታ ዓለማዊ ሁኔታን ለመፍጠር ጥረት አድርጋለች፡፡ ነገር ግን ይህ አዝማሚያ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ፣ ፋይናንስ እና ፖለቲካ ላይ ያለው ሚና እና ተፅዕኖ በፍጥነት ላይ በማደግ በሚገኙ ታዳጊ ሀገራት ተነሳሽነት እና ንቅናቄ ምክንያት በየጊዜው እየተዳከመ የሚሄድበት አዲስ ዓለማዊ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ በቀጣዮቹ ዘመናት የዓለም አቀፍ ስርዓቱ ከአንድ ዋልታነት ወደ ባለ ብዙ ዋልታነት ትራንስፎርም እያደረገ እንደሚሄድ ጠቋሚ የሆኑ ክስተቶችና አዝማሚያዎች በመፈጠር ላይ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ደኅንነት ላይ ቁልፍ ሚና የመጫወት አቅማቸውን በማሳደግ ላይ የሚገኙ ታዳጊ ሀገራት ጥምረት የሆነው ብሪክስ ንቅናቄ የዚህ የዓለም አቀፍ ስርዓት (world order) ትራንስፎርሜሽን አንዱ አመላካች ነው፡፡ የዚህ ጥምረት አባላትም ብራዚል፣ ራሺያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን የምዕራባዊያን አሉታዊ የሆኑ ፕሮፓጋንዳዎች፣ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች እና አሉባልታ ላይ የተመሠረቱ ወቀሳዎች በስፋት ቢስተዋሉም የብሪክስ ጥምረት ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት እየተጠናከረ እና ደረጃ በደረጃ አዎንታዊ ለውጦችን እያስመዘገበ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያ አካባቢ በንግድ እና ኢኮኖሚ ላይ ታጥሮ የነበረው የጥምረቱ ትኩረት በአሁኑ ወቅት እንደ ልማት፣ ኢነርጂ፣ ዓለም አቀፍ ፋይናንሳዊ ጉዳዮች እንዲሁም እንደ ሽብርተኝነት፣ ግጭቶች፣ የድንበር አለመግባባቶች፣ የወታደራዊ ኃይል አጠቃቀም፣ የኑክሊየር መሣሪያዎች ጉዳይ፣ የተደራጀ ወንጀል፣ የሳይበር ወንጀል፣ ድህነት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ችግሮች፣ የአካባቢ አየር ፀባይ ለውጥ እና ሌሎች የዓለም አቀፍ ደኅንነት ጉዳዮችን ወደ መዳሰስ በመስፋት ላይ ነው፡፡

የዓለም አቀፍ ደኅንነት ጉዳይ በዋና ዋና የዓለማችን ተቋማት እና ጥምረቶች ቁልፍ የሆነ የውይይት አጀንዳ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ብሪክስ የተለየ አይደለም፡፡ በዚህ በምንገኝበት ዘመን የዓለማችንን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ሐላፊነት የተሰጣቸው ተቋማትና ዋና ዋና የሚባሉ ተዋንያን ከዘመናዊው ዓለም እውነታዎች ጋር የማይጣጣሙ እንቅስቃሴዎች እና እርምጃዎች ላይ የተሠማሩ በመሆናቸው  የዓለማችን ደኅንነት በአግባቡ የማይሠራበት ሁኔታ እየተስተዋለ ይገኛል፡፡  የዚህ መሠረታዊ መነሻዎች ሀያላን የሚባሉ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ዓለም አቀፋዊ ስርዓቱ ከወቅቱ ጋር በሚስማማ መልኩ እንዲለወጥ የማይፈቅዱ እና እንዲሻሻል ፍላጎት የሌላቸው ከመሆኑ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ሀያላን ሀገራት በታዳጊ ሀገራት ላይ ከልክ ያለፈ ተፅዕኖ በማሳረፍ ብዛት ያላቸው ጥቅሞች እና ዕድሎች የሚያግበሰብሱበት ስርዓት መለወጥ በጥቅማቸው ላይ አሉታዊ አንድምታ አለው ብለው ማመናቸውና ይህንን መሠረት ያደረገ ግትርነት በመያዛቸው የተነሣ ዓለም አቀፍ ስርዓቱ ብዝበዛና ኢ - ፍትሐዊነት የነገሰበት እና በግጭቶች የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከዚህ አንፃር የብሪክስ ጥምረት አዲስ ዓለም አቀፋዊ ጉልበትን ይዞ የመጣ ሲሆን፤ በቀጣይ ዓለም አቀፍ ስርዓቱን የመለወጥ እምቅ ዐቅም ያለው ነው፡፡

የብሪክስ ሀገራት ጥምረት በዓለም አቀፍ ደኅንነት ላይ ያለው አንድምታ ሁለት ገጽታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ገፅታ ዓለም አቀፋዊ ገፅታ (the global dimension) ሲሆን፤ ሁለተኛው አካባቢያዊ ገፅታ (the regional dimension) ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የብሪክስ ሀገራት በዓለም አቀፍ ስርዓቱ ያላቸው ሚናን ከታዳጊ ሀገራት እንድምታ አንፃር የሚዳስስ በመሆኑ ዓለም አቀፋዊ ገፅታው ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ዋና ዋና የሚባሉ የጥምረቱ ዓለም አቀፋዊ ገፅታዎች ከዚህ ቀጥሎ እናያቸዋለን፡፡

የብሪክስ አባል ሀገራት እና ጥምረቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅና በማረጋገጥ ረገድ ቁልፍ ሚና አለው የሚለውን እሳቤ የሚደግፉ ናቸው፡፡ ጥምረቱ ዓለም አቀፋዊ የሰላም ግንባታ እና የሰላም ማስከበር ሥራዎች ማለትም አስቀድሞ የመከላከል (preventive deployments) እና ድኅረ ግጭት ሰላም ግንባታ (post – conflict peace building) ጥረቶች የተባበሩት መንግሥታት መመስረቻ ቻርተርን እና ተቀባይነት ያገኙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሕጎችን ባከበረ እና ባረጋገጠ መልኩ መሆን አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለው፡፡ የብሪክስ ጥምረት እንደ ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነፃነት፣ የግዛት አንድነት፣ ግጭትን ማስወገድ እና እኩልነት የመሳሰሉ ዓለም አቀፋዊ መርሖች እንዲከበሩ በመታገል ላይ ይገኛል፡፡

  1. ብሪክስ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፎርም

ከዚህ ባሻገር ጥምረቱ የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማዊ ሁኔታዎች ዙሪያ የሚካሄድ አጠቃላይ እና ሁሉን አቀፍ ሪፎርም አስፈላጊነት ላይ ጠንካራ አቋም በማንፀባረቅ ላይ ናቸው፡፡ የቻይና እና ራሺያ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባልነት እንዳለ ሆኖ ህንድ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ ሀገራት በምክር ቤቱ ላይ የበለጠ ሚና እንዲኖራቸው ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ የዚህ ጥምረት አባል የሆኑ ሀገራት ከሌሎች ሀገራት ጋር በመተባበር የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባልነት ከዚህ አሁን ካለው በላይ እንዲሰፋ ዓለም አቀፋዊ የሆነ ንቅናቄ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ የዚህ ንቅናቄያቸው አንዱ መነሻ ምክንያት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቋቋመው ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ተከትሎ በመሆኑ እና አሁን ያለው ዓለማዊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መቀየሩ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት ቁጥር ከ113 ወደ 193 ማደጉ ሌላኛው የሪፎርሙ አስፈላጊነትን የሚያነሱበት ምክንያት ነው፡፡

ሌላው የሪፎርሙ አስፈላጊነት የሚያሳየው ምንም እንኳን በጸጥታው ምክር ቤት በየጊዜው ከሚታዩ ጉዳዮች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአፍሪካ ሀገራትን የሚመለከቱ ቢሆንም አንድም የዚህ አህጉር ሀገር የምክር ቤቱ ቋሚ አባል አለመሆን ጋር ይያያዛል፡፡ ከዚህ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የግጭቶች መበራከት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት እነዚህን ግጭቶች ከመከላከል እና ከመቆጣጠር አንፃር በቂ እርምጃ አለመውሰድ የተቋማቱን አደረጃጀትና አሠራር ያረጀ እና ከጊዜው ጋር የማይሄድ ባሕሪ (anachronistic character) ያለው መሆኑ መጋለጡ ሪፎርሙን የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል ብለው ያምናሉ፡፡

የጸጥታው ምክር ቤት የ1945 እ.አ.አ ዓለምን እንጂ ከወቅቱ ጋር በሚሄድ ደረጃ ላይ አይደለም የሚል ተደጋጋሚ የሆነ ትችት በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የጸጥታው ምክር ቤት ሪፎርም ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ቁልፍ አጀንዳ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ አህጉራዊና ቀጠናዊ ተቋማት የጸጥታው ምክር ቤት አወቃቀር እንዲሰፋ እና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ስፋት ያላቸው ተፅዕኖዎችን በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በዚህ የምክር ቤቱ ሪፎርም አጀንዳ ዙሪያ በንቃት በመንቀሳቀስ ከሚገኙ ዓለም አቀፋዊ አደረጃጀቶች መካከል የብሪክስ ጥምረት ዋነኛ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

የብሪክስ ጥምረት አባል ሀገራት የጸጥታው ምክር ቤት ሪፎርም መደረግ አለበት የሚል እምነት ከመያዛቸው በተጨማሪ የምክር ቤቱ ቋሚ አባል የሆኑት ቻይና እና ራሺያ ይህንን የሪፎርም ጥሪ መደገፍ እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ የጥምረቱ የፀጥታው ምክር ቤት ሪፎርም ጥያቄ ምክር ቤቱ የበለጠ ውጤታማ፣ አካታች እና ሁሉንም የዓለማችን ሕዝቦች የሚወክል መሆን አለበት ከሚል ዓላማ የሚነሣ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በተባበሩት መንግሥታት እንደ አጠቃላይ እና በጸጥታው ምክር ቤት በተለይ የሚደረጉ ሪፎርሞች ታዳጊ ሀገራት በድርጅቱና በምክር ቤቱ ዙሪያ ያላቸውን ድምፅ እና ተሰሚነት ለማሳደግ የሚያስችል እና በተለይ የአፍሪካ ሀገራት በተደጋጋሚ በአጀንዳነት በሚያነሱበት ምክር ቤት ውስጥ ጥቅማቸውን የሚያስከብር ውሳኔዎች እንዲወሰኑ ለማድረግ የሚያግዝ ተሰሚነት እንዲኖራቸው ያደርጋል ተብሎ ይታመናል፡፡

  1. ብሪክስ እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርም

ሌላው ዓለም አቀፍ ገፅታው ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና ዓለም ባንክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምንም እንኳ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ድርሻ እና የምርት መጠን ከ50 በመቶ በላይ ቢሆንም በእነዚህ ተቋማት ያላቸው ድምፅ ግን እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ታዳጊ ሀገራት በእነዚህ ሁለት የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ተቋማት ላይ ያላቸው ተሰሚነት እና ድምፅ መጨመር አለበት የሚል መከራከሪያ የብሪክስ ሀገራት አንዱ አጀንዳ ሆኖ እየሠሩበት ይገኛል፡፡ ለዚህ የጥምረቱ ጥያቄ እና የታዳጊ ሀገራት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ አይኤምኤፍ እ.አ.አ 2009 የተወሰኑ ሪፎርሞችን ያደረገ ሲሆን፤ እነዚህም የታዳጊ ሀገራት ኮታ የመጨመር፣ በተቋሙ የዳይሬክተሮች ቦርድ የበለፀጉ ሀገራት ጥቅሞችንና ተሰሚነቶችን የመቀነስ፣ የዳይሬክተሮች ምርጫ አዳዲስ አሠራሮችን የማስተጋባት የመሳሰሉ ለውጦች ይገኙበታል፡፡ ምንም እንኳ የብሪክስ ሀገራት ጥረትና ተፅዕኖ እነዚህ ታዳጊ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ለውጦችን ለማምጣት ያስቻለ ቢሆንም፤ አብዛኛዎቹ በአሜሪካ ኮንግረስ ባለመፅደቃቸው ምክንያት ተፈፃሚነታቸው እምብዛም ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የብሪክስ ጥምረት በምዕራቡ ዓለም የተመሠረቱ እና የሚተዳደሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ነፃነትን ለማረጋገጥ አዋጪው መንገድ አማራጭ የሆኑ ተቋማት መመስረት መሆኑን በመገንዘብ በዚህ ላይ አተኩሮ በመሥራት ላይ ነው፡፡ የዚህ ቁልፍ ማሳያዎች እ.አ.አ 2014 ፎርታሌዛ ብራዚል ውስጥ በነበረው የጥምረቱ ጉባኤ ላይ የፀደቁት የአዲስ ልማት ባንክ መመስረት እና የሀገራት ገንዘብ ክምችት ፑል (Currency Reserves Pool) ይገኙበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዓለም ባንክ ተፎካካሪ ሊሆን የሚችለው የብሪክስ አዲስ የልማት ባንክ (New Development Bank) መቋቋም የጥምረቱን ተቋማዊነት ለማረጋገጥ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ተቋም ወደመሆን ለማሸጋገር የመጀመሪያው እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ የአዲሱ የልማት ባንክ መቋቋም ተነሳሽነት የብሪክስ ጥምረት ዓለም አቀፍ ልማትን ለማሳደግ ያለው ፍላጎትን የሚያንፀባርቅ ሲሆን፤ በተለይ በታዳጊ ሀገራት ልማት ዙሪያ ዋና ዋና ቅደም ተከተሎች ምን መሆን አለባቸው የሚለውን በትክክል ለመለየት ያለመ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወቅታዊ በባንኩ ዙሪያ ያሉ መረጃዎች የሚያሳዩትም የብሪክስ አዲሱ የልማት ባንክ በዋነኝነት ለታዳጊ ሀገራት የመሠረተ  ልማት ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጉ የፋይናንስ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱም ጥምረቱ በአፍሪካና ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ዘላቂነት ያለው ዕድገትና ልማት ማረጋገጥ የሚቻለው በመሠረተ ልማት ላይ በሚደረገው ኢንቨስትመንት ነው የሚል እምነት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ የታዳጊ ሀገራት ዋነኛው ተግዳሮት ከመሠረተ ልማት ግንባታ እና አቅርቦት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ነገር ግን የመሠረተ  ልማት የፋይናንስ ድጋፍ በእነ ዓለም ባንክ ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ ባለመሆኑ የአዲሱ ልማት ባንክ መቋቋም አስመልክቶ የአፍሪካ ሀገራት የብሪክስ አባል የሆኑ ሀገራት ያላቸው ከፍተኛ የሆነ የሀብትና የፋይናንስ ክምችት የአህጉሪቱን የመሠረተ  ልማት ዘርፍ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋን እንዲሰንቁ አድርጓል፡፡ ይህም ታዳጊ ሀገራት ከአላስፈላጊ ቅድመ - ሁኔታዎች እና ጣልቃ ገብነቶች የፀዳ አማራጭ የልማት ፋይናንስ ድጋፍ ምንጭ እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡

  1. ብሪክስ፣ ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ እና ዓለም አቀፍ ደኅንነት

ከዓለም አቀፍ ገፅታው ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት የብሪክስ ሀገራት እንድምታ የጥምረቱ አባል ሀገራት በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ዙሪያ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው፡፡ የጥምረቱ አባል ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮችን በማቅረብ እና የሰላም አስከባሪ ሥልጠናዎችን በስፋት በማቅረብ ከፍተኛ የሆነ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡ የጥምረቱ አባል የሆነችው ህንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰላም አስከባሪ ሠራዊት በማዋጣት በሦሥተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የብራዚል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቁልፍ አጀንዳ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ በተለይም በአፍሪካ አህጉር ዋና የሰላም ማስከበር ኦፕሬሽን ተዋናይ ናት፡፡ ቻይና የተባበሩት መንግሥታት ሰላም ማስከበር ኦፐሬሽን ዋነኛ የፋይናንስ ድጋፍ እና ሠራዊት አቅራቢ ስትሆን ራሺያ በበኩሏ የተለያዩ አውሮፕላኖችን እና ሄሊኮፕተሮችን በማቅረብ የድርጀቱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በመደገፍ የራሷ የሆነ አስተዋፅዖ ታበረክታለች፡፡

በዓለም አቀፍ ደኅንነት እየተስተዋለ የሚገኘው የመከላከል መብት (Responsibility to Protect - R2P) በሚል ፅንሰ ሐሳብ ሽፋን የሚካሄደው የምዕራባዊያን ሀገራትን ጣልቃ ገብነት በመገዳደር ረገድ የብሪክስ አባል ሀገራት የሚያደርጉት አስተዋፅዖ ሌላኛው የጥምረቱ የዓለም አቀፍ ገፅታ ማሳያ ነው፡፡ ምዕራባዊያን ሀገራት ግጭትን ለመከላከል እና ሰብአዊ መብትን ለማስከበር በሚል በሌሎች ሀገራት ላይ የሚያደርጓቸውን ጣልቃ ገብነቶች ጥምረቱ አጥብቆ ይኮንናል፡፡ ምዕራባዊያን ሀገራት ይህንን ፅንሰ ሐሳብ ፀረ ምዕራባዊያን ያሏቸው እና የምዕራባዊያንን ጥቅም በማያስጠብቁ መንግሥታት ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደ ምክንያት እየተጠቀሙበት የሚገኙ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የብሪክስ ሀገራት ይህንን የምዕራባዊያን አካሄድ በመቃወም ረገድ ጠንካራ አቋም አላቸው፡፡ ጥምረቱ ማንኛውም ግጭት ወታደራዊ ከሆኑ አማራጮች ውጭ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፈታት አለበት የሚል ፅኑ እምነት ያለው ሲሆን፤ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እና በግጭት ተዋንያን መካከል በሚካሄድ ሁሉን አቀፍ ውይይት ለግጭቶች መፍትሔ መፈለግ አለበት የሚል ዓለም አቀፋዊ ንቅናቄ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ በተለይ በታዳጊ ሀገራት ደኅንነት ላይ አዎንታዊ እንድምታ ያለው ነው፡፡

የብሪክስ አባል ሀገራት ሽብርተኝነትን አጥብቀው የሚኮንኑ ሲሆን፤ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ጠንካራ ዓለም አቀፋዊ ትብብር እና ቅንጅት እንዲኖር የሚያስችል የዓለም አቀፍ ፀረ ሽብር ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲጸድቅ እና በሁሉም ሀገራት ተግባራዊ እንዲሆን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ስርጭት ዙሪያም ጠንካራና ተራማጅ እሳቤን በማራመድ ላይ ሲሆኑ፤ በዓለም አቀፍ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች፣ ቴክኖሎጂዎች እና ቁሶች ምርትና ስርጭት ጠንካራ ቁጥጥር ለማካሄድ የሚያስችሉ አሠራሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ እነዚህ የጥምረቱ እይታዎችና አቋሞች የታዳጊ ሀገራትን ደኅንነት እና ጥቅሞችን በማረጋገጥ በኩል የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

  1. መደምደሚያ

ከቅኝ ግዛት የወጡ የአፍሪካ ሀገራት ምንም እንኳ ፖለቲካዊና ግዛታዊ ነፃነት አግኝተዋል ቢባልም የኢኮኖሚና የፖሊሲ ነፃነትን መጎናፀፍ አልቻሉም፡፡ ልዕለ ሀያል በሆነችው አሜሪካ የሚመራው የምዕራቡ ዓለም አዲስ የቅኝ ግዛት መልክ ይዞ በመምጣት በእነዚህ ታዳጊ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ እጁን በረጅሙ አስገብቶ እንደፈለገው ሲፈተፍት ቆይቷል፡፡

ነገር ግን ባለፉት ሁለት ዓሥርት ዓመታት በዓለማችን ፈጣን የሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብ ላይ የሚገኙ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኗቸው በማደግ ላይ የሚገኙ የብሪክስ ሀገራት በዓለም አቀፍ ስርዓቱ ውስጥ አዲስ አማራጭ ኃይሎች ሆነው ብቅ በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ጥምረት በአምስተኛ ጉባኤው ላይ ሁሉንም ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ያካተተ ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ እነዚህም የዓለም አቀፍ ደኅንነት፣ ልማት፣ የዓለማችን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ወዘተ… ናቸው፡፡ በዚህም አማካኝነት በአሁኑ ወቅት በምዕራባዊያን ከፍተኛ ተፅዕኖ ስር የሚገኘው የዓለም አቀፉ ስርዓትና መዋቅር የሁሉንም የዓለማችን ሀገራት እና ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ለመቀየር እና ለማሻሻል የብሪክስ ጥምረት ያላቸውን ዐቅም አስተባብረው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡  የዚህ ጥምረት አጠቃላይ እንቅስቃሴም ዓለም አቀፋዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስርዓቱ ባለብዙ ዋልታነት፣ ፍትሀዊነት፣ ሚዛናዊነት እና ዴሞክራሲያዊነት በመሳሰሉ መርሖች እንዲመራ ማድረግ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ታዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ ስርዓቱ ላይ ያላቸው እይታና ጥቅም የበለጠ ተደማጭ የሚሆንበት ዕድል ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከዚህ ባሻገር  ሰላማዊ በሆነ መንገድ እና ደረጃ በደረጃ በሚካሄድ ሪፎርም አማካኝነት ዓለም አቀፍ ተቋማት የበለጠ ወካይ፣ አሳታፊ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል የተባበረ ተፅዕኗቸውን ለማሳረፍ እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ የእነዚህ ሀገራት ጥምረት ታዳጊ ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግም ሆነ ብሔራዊ ደኅንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል፤ ከሀገራቱ ሁኔታ ጋር የስነ ልቦና ትስስር ያላቸው ሀገራት የተካተቱበት አማራጭ ዓለም አቀፍ አደረጃጀት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡

ታዳጊ ሀገራት ከዚህ ጥምረት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? ይህንን ጥምረት በመጠቀም ታዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ ስርዓቱ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅማቸውን በምን መልኩ ለማስጠበቅ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል? የሚሉ ጥያቄዎች የሀገራቱ መንግሥታት ብልህ የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲዎችን እና ጥበብ የተሞላባቸው ስትራቴጂዎችን መቅረፅ እና ተግባራዊ ማድረግ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የመሠረቱትንና "ብሪክስ" በሚል ስያሜ የሚታወቀውን ሕብረት በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የቡድኑ  አባል ሀገራት ጉባኤ መቀላቀሏ ይፋ ሆኗል፡፡ ብሪክስ ኢትዮጵያን ጨምሮ፥ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያን እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችን በአዲስ አባልነት የተቀበለ ሲሆን፤ ይህ አዲስ ጥምረት ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በምዕራቡ ዓለም ፍላጎቶችና ጥቅሞች መሠረት ሲነዳ የነበረው ዓለም አቀፍ ስርዓት በተለይ በታዳጊ ሀገራት ልማት፣ ኢኮኖሚ፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት እንድነት እና የፖሊሲ ነፃነት ላይ ዘርፈ ብዙ የሆኑ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንደሚቀንስ ይጠበቃል፡፡

የብሪክስ አባል ሀገራት በተለይ ቻይናና ሩሲያ  የጸጥታው ምክር ቤት ሪፎርም ማድረግ አለበት የሚል እምነት ያላቸው በመሆኑ ኢትዮጵያና ሌሎች ሀገራት ጥምረቱን መቀላቀላቸው በተደጋጋሚ የሚነሳው የአፍሪካ የውክልና ጉዳይ መፍትሄ እንዲሰጠው ግፊት መፍጠሩ አይቀርም፡፡ በዚህ አውድም የኢትዮጵያ ዲፖሊማሲያዊ ስኬት የራሱን አስተዋጽዖ ማበርከቱ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ  ከፍተኛ የሆነ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድልን በማስፋት፤ የውጭ ምንዛሪ መዋዥቅን በመቀነስ፤ ጂኦፖለቲካዊ ተጽእኖን በማሳደግ፤ የፋይናንስ ተቋማትን በማሳደግ ጉልህ ሚና ያበረክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም