ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በሁሉም አውድ ሊገጥማት ከሚችል ስጋት እና ጥቃት መመከት የሚችል የአገር ኩራትና አለኝታ የሆነ ዘመናዊ ሰራዊት ተገንብቷል - ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን  

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያን በሁሉም አውድ ሊገጥማት ከሚችል ስጋት እና ጥቃት መመከት የሚችል የአገር ኩራትና አለኝታ የሆነ ዘመናዊ ሰራዊት መገንባቱን የመከላከያ ሰራዊት ህብረት ስልጠና ዋና መመሪያ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን ገለጹ፡፡  

የኢፌዴሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅ በረጅም እና በአጭር ጊዜ ያሰለጠናቸውን 32 ከፍተኛ መኮንኖች አስመርቋል። 

ኮሌጁ ከተቋቋመበት 2011 ጀምሮ የተጣለበትን የሰለጠነ የሰው ሃይል የማፍራት ሀላፊነት በሚገባ እየተወጣ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሰራዊት ህብረት ስልጠና ዋና መመሪያ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን፤ ተመራቂዎች ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ መትጋት አለባቸው ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴር ለሰው ሃይል ግንባታ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በዚህም የአገር ኩራትና አለኝታ ሰራዊት መገንባቱን ተናግረዋል።

ሰራዊቱ ኢትዮጵያን በሁሉም አውድ ሊገጥማት ከሚችል ስጋት እና ጥቃት መመከት የሚችል ሰራዊት   ነው ብለዋል፡፡

በትምህርት እና ስልጠና በተሻለ ትጥቅ እና ብቁ አመራር ተቋሙን የማደራጀት ተግባር በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ በደህንነትና እስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ከፍተኛ አመራሮችን ለማብቃት እያከናወነ የሚገኘው የስልጠና ሂደትም እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

በዛሬው ዕለት የተከናወነው የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ምረቃም ኮሌጁ ተልዕኮውን በበቃት እየተወጣ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ተመራቂዎች በቆይታቸው ባገኙት ዕውቀት ሌሎች መኮንኖችን ለማፍራት መትጋትና የዕለት ተዕለት ስራዎቻቸውን በብቃት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
 

የኢፌዴሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ቡልቲ ታደሰ በበኩላቸው ኮሌጁ 19 መኮንኖች በመደበኛ አጭር ኮርስ እና 13 ከፍተኛ መኮንኖችን ደግሞ በስትራቴጂካዊ ደህንነት የስልጠና ዘርፎች አሰልጥኖ ማስመረቁን ገልጸዋል፡፡

ተመራቂዎች በቆይታቸው በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና አካባቢ ጥናት፣ በህብረት ዘመቻ፣ በስትራቴጂካዊ ደህንነት እና በስትራቴጂክ አመራር የትምህርት መስኮች እና በሌሎችም የክፍል እና የተግባር ልምምድ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ተመራቂ መኮንኖች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው በተሰማሩበት የሙያ መስክ አገራቸውን በብቃት ለመገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ወርቁ ከበደ በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው በተሰማሩበት የሙያ መስክ አገራቸውን በብቃት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮሎኔል አስታጠቅ አዳነ በበኩላቸው ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ባገኙት እውቀትና ክህሎት የአገራቸውን ዳር ድንበር የሚያስጠብቁ ብቁ አመራችን ለማፍራት እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ ኮሎኔል ወርቁ አሸናፊ ናቸው፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የመከላከያ ሰራዊት ህብረት ስልጠና ዋና መመሪያ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን፣ የመከላከያ የሰው ሃብት ዋና መመሪያ ሀላፊ ሌተናል ጄኔራል ሃጫሉ ሸለመን ጨምሮ ሌሎች የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ተገኝተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም