ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረኮች ያላት ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን ያመላከተ ነው-ቢልለኔ ስዩም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረኮች ያላት ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን ያመላከተ ነው-ቢልለኔ ስዩም
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረኮች ያላት ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን ያመላከተ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁማ በኢኮኖሚና ዲፕሎማሲ መስክ ያስመዘገበችው ስኬት ተደማጭነቷ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።
በዚህም በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬት የብሪክስ አዲስ አባል አገራት መሆናቸው ይፋ ተደርጓል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም፤ ባለፉት ጊዜያት በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና በባለብዙ ወገን መድረኮች ተገቢውን ስፍራ ለማግኘት ከፍተኛ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ እያስመዘገበች ያለው እድገት የዲፕሎማሲ አቅሟ እንዲጎለብት ማድረጉን ነው የጠቆሙት፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ፤ ይህም ከራሷ ባለፈ የአፍሪካን ጥቅም ለማስከበር እንድትሰራ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገራትን መቀላቀሏ በቡድኑ ውስጥ ካሉና ኢኮኖሚያቸው እያደገ ከመጡ ሀገራት ጋር በትብብር እንድታድግ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታየው ተለዋዋጭ አሁናዊ ሁኔታ ውስጥ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ድምጿን ለማሰማት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራችና ውጤት እያገኘች መሆኑን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የዓለም አገራትና ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ጋር ትስስር በመፍጠር አብሮ ለማደግ ያላቸውን ፍላጎት እያሳዩ መሆኑንም ጠቁመዋል።