"የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው" በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰት ነው--የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
"የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው" በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰት ነው--የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ "የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው" በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑን የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ።
በተመሳሳይ “የፋሲል ቅርስ በጎንደር ከተማ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጉዳት አድርሰውበታል” የሚል የተሳሳተ መረጃ ከሳምንታት በፊት ተሰራጭቶ ነበር ።
ይህን መረጃ ተከትሎም ኢዜአ በጎንደር ከተማ የዓለም አቀፍ ቅርሶች አስተዳደር ሀላፊ የሆኑት ጌታሁን ስዩምን ጠይቆ በቅርሶች ላይ ምንም የደረሰ ጉዳት አለመኖሩንና መረጃው ፍጹም ሀሰት መሆኑን ማረጋገጡ ይታወሳል።
አሁንም "የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው" በሚል አንድ ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ZeEthiop የተሰኘ የፌስቡክ ገጽ ትናንት መረጃ አጋርቷል።
"የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው" በሚል የተሰራጨውን የሀሰት መረጃ በተመለከተ የኢፕድ መረጃ ማጣሪያ ነዋሪዎችን እና አስጎብዎችን ከቦታው፤ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና ክልሉን አናግሯል።
ይህን መረጃ ተከትሎም የፕሬስ መረጃ ማጣሪያ የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌውን (ረዳት ፕሮፌሰር) በፌስ ቡክ የተሰራጨውን መረጃ ልኮላቸው እንደተመለከቱት ገልጿል።
ዋና ዳይሬክተሩ መረጃውን በተመለከተ በሰጡት ምላሽም "ባጭሩ የላካችሁልኝ መረጃ ትክክለኛ አይደለም" ብለዋል። በተባለውም ጊዜ ሆነ ከዚያ ውጭ የላሊበላ ቅርሶችን አደጋ ላይ የጣለ ምንም አይነት ክስተት አለመኖሩን ዋና ዳይሬክተሩ ማረጋገጣቸውን ኢፕድ አስነብቧል።
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓባይ መንግሥቴም በፌስቡክ የተጋራው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ለኢፕድ ተናግረዋል። "ትናንትም ሆነ ዛሬ በላሊበላ ከተማ በሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች ቱሪስቶች በሚፈለገው ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ፡" ሲሉም ገልጸዋል።
የላሊበላ አብያተክርስቲያናትም ሆነ ለአካባቢው ማሕበረሰብ ስጋት የሚሆን የጸጥታ መደፍረስም ሆነ የከባድ መሣሪያ ልውውጥ አለመኖሩን ምክትል ቢሮ ሀላፊው ማረጋገጣቸውን ኢፕድ በማጣሪያ አስነብቧል፡፡
በላሊበላ አብያተክርስቲያናት አካባቢው ከባድ መሣሪያ ተጠምዷል፤ ቅርሶችም አደጋ ውስጥ ነው በሚል የሚናፈሰው መረጃ ሀሰት መሆኑን ምክትል ቢሮ ሀላፊው ለኢፕድ የገለጹ ሲሆን ይህንኑ መረጃ በከተማው የአስጎብኝዎች ማኅበር አባላት ተረጋግጧል ብሏል።
"በከተማዋ ሰላም ሰፍኗል፤ ጎብኝዎችም ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን እየጎበኙ ይገኛል ሲሉ መግለጻቸውንም ገልጿል።
በየቀኑም የውጭ አገራት ቱሪስቶችን እየተቀበልን እያስተናገድን ነው ያሉት አስጎብኝዎች፣ የአየር በረራ መልሶ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከዛሬዋ እለት ድረስ የውጭ ጎብኝዎችን ሳናስተናግድ የዋልንበት ቀን የለም ሲሉም ለኢፕድ ተናግረዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎችም ቅርሱን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል የከባድ መሣሪያ ተኩስ በቅርሱ አቅራቢያ ተደረገ የተባለው መረጃ ሀሰት መሆኑን አስረድተዋል።
የላሊበላ አብያተክርስትያናት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩና የዓለም ጭምር ቅርስ በመሆናቸው መንግሥት እና የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ድጋፍ በማድረግ ጥበቃና እንክብካቤ ይደረግለታል።