ሚኒስቴሩ ለግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታው ጥናት ውጤታማነት አስፈላጊዉን ድጋፍ ያደርጋል--ዶክተር ግርማ አመንቴ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ ለግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታው ጥናት ውጤታማነት አስፈላጊዉን ድጋፍ ያደርጋል--ዶክተር ግርማ አመንቴ
ጋምቤላ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታው ጥናት ውጤታማነት አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ።
የጋምቤላ ክልል የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ይፋ ተደርጓል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በጋምቤላ ክልል ለግብርና ልማት ሊውል የሚችለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ወደ ልማት በመለወጥ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አመራሩ አርሶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩን አስተባብሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም በክልሉ ያለዉን ሰፊ የመሬትና የውሃ ሃብት ፀጋዎች በግብርና ቴክኖሎጂ በመደገፍ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በክልሉ ለግብርና ልማት ሊውል የሚችለውን ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ማልማት ከተቻለ ለክልሉ ህዝብ ብቻ ሳይሆን አገርን የመመገብ አቅም ያለው ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በክልሉ የተዘጋጀው የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናትም በአካባቢዉ ያሉትን ፀጋዎች የለየና ለግብርና ልማቱ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም የተዘጋጀውን የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናት በተጀመረው አዲሱ በጀት አመት ወደ ተግባር ለማስገባት አመራሩን፣ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን እና የዘርፉ ባለሙያዎችን በማስተባበር በትጋት መሠራት እንደሚኖርበት ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለግብርና ፍኖተ ካርታ ጥናቱ ውጤታማነት አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ዶክተር ግርማ አመንቴ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ በበኩላቸው በክልሉ ያለዉን የተፈጥሮ ሃብት በምርምር በመደገፍ በኩል ኢንስቲትዩቱ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በኢንስቲትዩቱ እና በክልሉ ግብርና ምርምር ተቋማት ትብብር ለተዘጋጀዉ የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ስኬታማነት አስፈላጊዉን እገዛ እንደሚያደርጉ ዶክተር ፈቶ ገልፀዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ አመራሮች በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ለተዘጋጀው የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናት ስኬታማነት ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በተቋማቱ የተዘጋጀውን የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናት ለክልሉ መንግስት አስረክበዋል።