የመሬትና የውሃ ሀብት በግብርና ቴክኖሎጂ በመደገፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረዉ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ሮት ጋትዊች - ኢዜአ አማርኛ
የመሬትና የውሃ ሀብት በግብርና ቴክኖሎጂ በመደገፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረዉ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ሮት ጋትዊች
ጋምቤላ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት በግብርና ቴክኖሎጂ በመደገፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ሮት ጋትዊች ገለጹ።
የክልሉ የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ይፋ ሆኗል።
ጥናቱን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የግብርና የሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናት ላይ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ተወካይ አቶ ሮት ጋትዊች፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት ጨምሮ ሌሎች የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
በክልሉ ለግብርና ልማት ምቹና ሰፊ እምቅ ሀብት ቢኖርም ከአሁን በፊት አርሶ አደሩ ዘመኑ ያፈራዉን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ውስንነቶች እንደነበሩ አቶ ሮት ገልጸዋል።
በመሆኑም አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን ከባህላዊ የአስተራረስ ዘይቤ በማላቀቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይም በግብርናው ልማት ላይ ይስተዋሉ የነበሩ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግሮችን ለማሻሻል በአዲሱ የለውጥ ምዕራፍ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የግብርና ሽግግር የፍኖተ ካርታው ጥናት የዚሁ ስራ አንዱ ማሳያ መሆኑን ነው ተወካዩ የጠቀሱት።
በክልሉ ያለዉን ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት በግብርና ቴክኖሎጂ በመደገፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አጃክ ኡጁሉ በበኩላቸው ክልሉ ለግብርናው ልማት የሚውል ምቹ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ያለበት አካባቢ መሆኑንና ይህንን ሀብት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማሳደግ መስራት ከተቻለ ከክልሉም አልፎ ለአገሪቱ የሚውል አቅም መኖሩን ገልጸዋል።
ከዚህም አኳያ የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ጥናት ወደ ተግባር በመቀየር የአርሶና የከፊል አርብቶ አደሩን ሕይወት ከመለወጥ ባለፈ ለአገር ኢኮኖሚ የድርሻውን ሚና እንዲወጣ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በቀረበው የጥናት ውጤት ላይ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።