የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው--የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው--የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ትልቅ አቅም የፈጠረ የለውጡ ትሩፋት ነው ሲም ነው አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ የገለጸው።
የብሪክስ ቡድን ኢትዮጵያ የቡድኑ አባል ለመሆን ያቀረበችውን ጥያቄ ተቀብሎ በደቡብ አፍሪካ ባካሄደው 15ኛ ጉባኤው ላይ ማጽደቁ ይታወሳል።
ይህንን በማስመልከትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደስታ መግለጫ አውጥቷል።
የከተማ አስተዳደሩ ሙሉ መግለጫውም እንደሚከተለው ይቀርባል ፦
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባልነት ጥያቄዋ ተቀባይነት በማግኘቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ የደስታ መግለጫ
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ ካቀረቡ 40 በላይ ሀገራት መካከል መስፈርቶችን ሁሉ አሟልታ ጥያቄዋ ተቀባይነት ማግኘቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰማውን ታላቅ ደስታ ይገልፃል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ያቀረበችው የዚህ ቡድን አባልነት ጥያቄ በቡድኑ አባል አገራት የተቀመጡ መስፈርቶችን ሁሉ ማሟላት በመቻሏ ሙሉ አባልነቷም ተቀባይነት ማግኘቱ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ትልቅ አቅም የፈጠረ የለውጡ ትሩፋት ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀደምትና ታላቅ ሀገር ናት። የአፍሪካ ሕብረት መስራችና መቀመጫ፣ በዓለም ሶስተኛዋ የአለም አቀፍ ተቋማት መናህሪያ እንዲሁም በቀኝ ግዛት ያልተገዛች፣ ባለ ብዙ ታሪክ፣ ትልቅ የህዝብ ቁጥር ያላት ግዙፍ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይ ሰንቃ ወደ ፊት እየገሰገሰች ያለች አገር ናት።
ሀገራችን ብሪክስን መቀላቀሏ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው፤ ይህ ድል መንግስት በዲፕሎማሲው መስክ የሰራቸው ስራዎች ውጤታማነት ማሳያ ነው፤ ከሁሉም ሀገራት ጋር ብሔራዊ ጥቅምንና ኩራትን ቀዳሚ ያደረገ በመርህ ላይ የተመሠረት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖር በላቀ ትጋትና ጥበብ በመሰራቱ ነው፡፡ በተለይ የክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን ዶክተር ዐቢይ አህመድ የውጪ ግንኙት ፖሊሲ አቅጣጫችንን በማስተካከል በላቀ ጥበብ፣ ትጋትና ቁርጠኝነት ለሰጡት ውጤታማ አመራር በከተማ አስተዳደራችንና ነዋሪ ስም ላቅ ያለ ምስጋና እናቀርባለን።
ኢትዮጵያ ሀገራችን የብሪክስ (BRICS) አባል አገር በመሆኗ ከምታገኛቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ውስጥ አንዱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ሲሆን በዚህም በተለይ ከአባል ሀገራት ጋር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ የቴክኖሎጂ እና የዕውቀት ሽግግርን በመፍጠር የሀገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገት በማፋጠን ወደ ብልፅግና የምናደርገውን ጉዞ የሚያፋጥን ብሎም የሚያግዝ በመሆኑ የተሰማን ደስታ የላቀ ነው።
የብሪክስ (BRICS) አባል ሀገራት ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደገ ያለ፣ ትልቅ የህዝብ ቁጥር እና ሰፊ የገበያ ዕድል ያላቸው ከመሆኑ አንፃር ኢትዮጵያ ከዚህ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደምታገኝ እናምናለን።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የወጪ ንግዷን ታሳድጋለች፣ የንግድ ትስስሯን ታጎለብታለች፤ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የመሆን አቅሟን ከፍ ከማድረጉም በላይ ከአባል ሀገራቱ ጋር በመተባበር የመሰረተ ልማት ግንባታዋን እና አቅሟን የማሳደግ ዕድል የሚከፍት ትልቅ ድል ነው።
በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ ፣ በተለያዩ መድረኮች ላይ ፍትህ እና ርትዕ እንዲሰፍን ሀገራችን የበኩሏን ሚና መወጣት የሚያስችላት ከመሆኑም በላይ የሚደርሱባትን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ጭምር እንድትቋቋም የሚያግዝ ትልቅ ስኬት ነው።
በአጠቃላይ ሀገራችን የብሪክስ አባል መሆኗ በዲፕሎማሲው መስክ ያገኘነው ድል ትልቅ ድል ነው። ይህንን ድል እንደ ስንቅ ተጠቅመን በሀገራችን ሰላምን በማስፈን፣ ልማትን በማፋጠን እና በተለይ ደግሞ የጀመረነውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በጥሩ መሰረት ላይ አደላድለን በማኖር የልማት ጉዟችንን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል።
በመጨረሻም የሀገራችን ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባልነት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ ትልቅ ሚና ለተጫወቱት አባል አገራት ለቻይና፣ ለሩሲያ፣ ለብራዚል፣ ለህንድ እንዲሁም ለደቡብ አፍሪካ መንግስታት የላቀ ምስጋናችንን በከተማ አስተዳደሩና በከተማችን ህዝብ ስም እናቀርባለን።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ!
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
ነሐሴ 20/ 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ