ቀጥታ፡

በሴቶች ማራቶን የተገኘውን ድል ተከትሎ ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ አለች

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ በሀንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ ባለው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴቶች ማራቶን የተገኘውን ድል ተከትሎ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ከነበረችበት ስድስተኛ ደረጃ ወደ አራተኛ ከፍ ማለት ችላለች።

ዛሬ ረፋድ ላይ በተካሄደው የሴቶች ማራቶን ውድድር አትሌት አማኔ በሪሶ 2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ ከ23 ሴኮንድ በመግባት ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

አትሌት ጎይተቶም ገብረስላሴ 2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ ከ34 ሴኮንድ ሁለተኛ የብር ሜዳሊያ ለአገሯ ማስገኘት ችላለች።

አትሌት ጎይተቶም እ.አ.አ በ2022 በአሜሪካ ኦሬጎን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።

ሞሮኮዋዊቷ አትሌት ፋጢማ ጋርዳዲ 2 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ከ17 ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥታለች።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቅቃለች።

በውድድሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቶች የቡድን ስራ ለውጤቱ መገኘት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን አትሌቶቹ የመረዳዳት፣ የመደጋገፍና የአብሮነትን መንፈስ አሳይተዋል።

ውጤቱንም ተከትሎ ኢትዮጵያ 2 የወርቅ፣ 4 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከነበረችበት ስድስተኛ ደረጃ ወደ አራተኛ ከፍ ብላለች።

አሜሪካ፣ ስፔንና ጃማይካ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

በተያያዘም ዛሬ ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ50 የ5 ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ይደረጋል።

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ፣ እጅጋየሁ ታዬ፣ መዲና ኢሳ እና አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው።

አትሌት ጉዳፍ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር የወርቅ እንዲሁም አትሌት እጅጋየሁ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም