ቀጥታ፡

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የስምንተኛ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ የምትወዳደርባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ይደረጋሉ።

ከማለዳው ሁለት ሰዓት የሴቶች ማራቶን ውድድር እየተከናወነ ነው።

በውድድሩ ላይ አትሌት ጎይቲቶም ገብረስላሴ፣አማኔ በሪሶ፣ ፀሐይ ገመቹና ያለምዘርፍ የኋላው ይሳተፋሉ።

አትሌት ጎይቲቶም እ.አ.አ በ2022 በአሜሪካ ኦሬጎን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይም ዛሬ ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ50 የ5 ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ይደረጋል።

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ፣እጅጋየሁ ታዬ፣ አትሌት መዲና ኢሳና አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው።

አትሌት ጉዳፍ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር የወርቅ እንዲሁም አትሌት እጅጋየሁ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘታቸው ይታወቃል።

በተያያዘም ትናንት ማምሻውን በ800 ሜትር ሴቶች የግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያ የተወዳደሩት አትሌት ሀብታም ዓለሙ እና አትሌት ወርቅነሽ መለሰ ከየምድባቸው በተመሳሳይ አራተኛ በመውጣት ወደ ፍጻሜው ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሃንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ ባለው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ እስከ አሁን 1 የወርቅ፣ 3 የብር እና 2 የነሐስ በአጠቃላይ ስድስት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ሻምፒዮናው ነገ ይጠናቀቃል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም