ቀጥታ፡

የአቪዬሽን ዘርፉን በጠንካራ መሰረት ለማስቀጠል በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 19/2015 (ኢዜአ) ፦ የአቪዬሽን ዘርፉን በጠንካራ መሰረት ለማስቀጠል በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩንቨርሲቲ ከመላው ኢትዮጵያ ለተውጣጡ የሁለተኛ ደረጃ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ለ6 ሳምንታት የሰጠው ስልጠና ዛሬ ተጠናቅቋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ካሴ ይማም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪዬሽን ትምህርት ዘርፍ የተሳካ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከመላው ኢትዮጵያ ለተውጣጡ 24 የተፈጥሮ ሳይንስ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በዩንቨርሲቲው የተሰጠው ስልጠና በቀጣይ በአቪዬሽን ዘርፍ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በስልጠናው የተሳተፉ ተማሪዎችም ለወደፊት ለሚሰማሩበት የሙያ መስክ ጥሩ መሰረት የሚያሲዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጅነሪንግና የሂሳብ ትምህርቶች በተግባር የተደገፉ ሲሆኑ ወጣቶችን ለበለጠ የፈጠራ ስራ የሚያነሳሱ በመሆኑ ስልጠናው የላቀ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

በመሆኑም የአቪዬሽን ዘርፉን በጠንካራ መሰረት ለማስቀጠል በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ፤ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጅነሪንግና በሂሳብ ትምህርቶች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።


 

ሚኒስቴሩም ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የስልጠናው ተሳታፊ ተማሪዎች በበኩላቸው በቆይታቸው ለቀጣይ ህይወታቸው የሚጠቅሙ በርካታ ልምድና ተሞክሮዎች ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው እድሉን ላመቻቹ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ስልጠናው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ፣ በቦይንግ ኩባንያና ቲንክ ያንግ አፍሪካ በተሰኘ የወጣቶች ዲጂታል ዓለም ማሰልጠኛ ተቋም የጋራ ትብብር የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም